የኢህአዴግ መንግስት የስለላ ስራ ለሚሰራለት ለአንድ ኩባንያ ብቻ 1 ሚሊዮን ዶላር ከፈለ

ሰኔ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጣሊያን ውስጥ የሚገኘውና ሃኪንግ ቲም ” hacking team” በመባል የሚታወቀው ለደህንነትና ለስለላ የሚያስፈልጉ የኮምፒዩተር ሶፍት ዌሮችን የሚሸጠው ድርጅት፣ የራሱ መረጃዎች በሌሎች ሃይሎች የተዘረፈ ሲሆን፣ እስካሁን ይፋ በሆኑት መረጃዎችን ቢንያም ተወልደ የተባለ ኢትዮጵያዊ በብሄራዊ ስለላ ድርጅት ስም 1 ሚሊዮን ዶላር በአንድ ጊዜ መክፈሉን የወጣው ሰነድ ያመለክታል።
ገንዘቡ የተከፈለው በቀጥታ ከመንግስት የስለላ ተቋም ነው። ከዚሁ ድርጅት ጋር ግንኙነት ያለው ይህ ቢኒያም የተባለው ግለሰብ ፣ ድርጅቱ አንድ ቁልፍ ተጠርጣሪን ለመሰለል እንደረዳው በመግለጽ ምስጋናውን አቅርቧል።
ከዚህ ቀደም ሲትዝን ላብ የሚባለው የካናዳ ኩባንያ የኢህአዴግ መንግስት የኢሳት ጋዜጠኞችን ለመሰለል የሚጠቀምበትን የስለላ ሶፍት ዌር ጣሊያን ከሚገኘው ሃኪንግ ቲም ማግኘቱን አጋልጦ ነበር።
ኢህአዴግ ፊን ፊሸር የተባለውን የስለላ ሶፍት ዌር የእንግሊዝና ጀርመን ንብረት ከሆነው ጋማ ኩባንያ መግዛቱ መዘገቡ ይታወቃል።