የኢህአዴግ መንግስት በድርቅ ለተጎዱት ወገኖች የእርዳታ ጥሪ አቀረበ

ነኅሴ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚታተመው ሳምንታዊ የሰብአዊ እርዳታ መጽሄት እንደዘገበው መንግስት በአገሪቱ ውስጥ የታየውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ለጋሽ አጋራት አስቸኳይ እርዳታ እንዲለግሱ ጥሪ አቅርቧል። ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ሊፈጠርባቸው ይችላል ተብሎ ለተሰጋባቸው ቦታዎች መንግስት 700 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቋል። ዞን 3 በሚባለው የአፋር አካባቢ እንዲሁም ስቲ ዞን በሚባለው የሶማሊያ ክልል አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ዘገባው አመልክቷል። በመላ አገሪቱ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልገው ህዝብ ቁጥር 9 በመቶ ጨምሯል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኦሮምያ፣ ከፊል አማራና በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎችም ድርቅ ተከስቷል። ድርቁ እስከ ጥቅምት ሊዝልቅ እንደሚችል የሜትሮሎጂ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ባለሙያዎች እየገለጹ ነው።
በአፋር ክልል በተለይ ዜጎች በውሃ እጥረት እየተቸገሩ ሲሆን፣ በርካታ የቀንድና የጋማ ከብቶች በድርቁ ምክንያት አልቀዋል።
በደቡባዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በዶዶላ ወረዳ ዝናብ መጣሉን በማቆሙ መሬቱን ታርሶ በሰብል አለመሸፈኑን እና የአካባቢው አርሶ አደሮችም በስጋት ውስጥ እንዳሉ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።