ሰኔ ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ዛሬ ለፓርላማ አባሎች እንደተናገሩት የኤርትራ መንግስት አካባቢውን የማተራማስ አጀንዳውን ካላቆመ ፣ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
አቶ ሃይለማርያም ሻእቢያ ኢትዮጵያና ጅቡቲን ለማተራመስ እየሰራ ነው ሲሉ ከሰዋል። የኢትዮጵያን ህዝብ አስታውቀን እርምጃ እንወስዳለን ያሉት አቶ ሃይለማርያም፣ እስካሁንም ለደረሰብን ጥቃት ተመጣጣኝ እርምጃ ስንወስድ ቆይተናል ሲሉ አክለዋል።
የአቶ ሃይለማርያም መግለጫ በቅርቡ የአርበኞች ግንቦት7 ሰራዊት በሰሜኑ አገሪቱ ክፍል በኢህአዴግ ወታደሮች ላይ ወታደራዊ ጥቃት በመፈጸም ፣ ድል ማግኘቱን ባስታወቀ ማግስት ነው።
አርበኞች ግንቦት7 ሰራዊት በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት፣ በርካታ የስርአቱ ወታደሮች መገደላቸውን ገልጿል።
ይህንን ተከትሎ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የታዩ ሲሆን፣ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ምናልባትም ከኤርትራ መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚለውን ግምት ከፍ አድርጎታል።
ምንም እንኳ ለዲሞክራሲና ለነጻነት የሚታገሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች መነሻቸውን ኤርትራ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመሻገር ጥቃቶችን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ቢያመለክቱም፣ ኢህአዴግ ግን እውቅና ለመስጠት አልፈለገም። ችግሩ እየገፋ በመምጣቱ ማስተባበል ያልቻለው ኢህአዴግ፣ ችግሩን ከኤርትራ መንግስት ጋር በማያያዝ ለዲሞክራሲና ለነጻነት የሚደረገውን ትግል፣ ውጫዊ ምክንያት ሊሰጠው ይፈልጋል ሲሉ ተቃዋሚዎች ይተቻሉ።
ገዢው ፓርቲ ወታደሮችን ለመመልመለስ ተደጋጋሚ ማስታወቂያዎችን ያወጣ ቢሆንም፣ ከወጣቱ በኩል የሚሰጠው ምላሽ አሉታዊ ሆኖበታል። በተለያዩ ስልጠናዎች ስም ወጣቱን ወደ ወታደራዊ ካምፖች ለማጋዝ እንቅስቃሴ መጀመሩንም የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሌላ በኩል አርበኞች ግንቦት7 ትን ለመቀላለቀል የሚጠይቁ ወጣቶች መበራከታቸውን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ድርጅቱ ወጣቶች ባሉበት ሆነው እንዲደራጁ ቢጠይቅም፣ ወደ ግንባር ለመቀላቀል የሚፈልጉ ወጣቶች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ መምጣቱን አስታውቋል።