መጋቢት ፳፪ (ሃይ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ባሳለፍነው ሳምንት ከፍተኛ ተነባቢነትን ያለውን የፍትህ ጋዜጣ ድህረ ገጽ መዘጋቱን ተከትሎ በዚህ ሳምንት ደግሞ የተለያዩ ብሎጎች እና ድህረ ገጾች ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ከቻይና መንግስት የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር በመተባበር ዌብሳይቶችን እንዲዘጋ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ
የሚዲያን ሃያልነት እና ልዩ ጠቀሜታን ጠንቅቆ እንደተረዳው ያስገነዝባል ። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግስት በአሁን ሰአት ከተለያዩ
አቅጣጫዎች የተፈጠረበትን ውጥረት ለማርገብ ሲል የነጻ ሚዲያዎችን ከነአካቴው ከድህረ ገጾች ላይ እንዲጠፉ ለማድረግ ቢሞክርም ሊሳካለት አልቻለም።
በትላንናው እለት ከተዘጉት ድህረገጾች መካከል አንዱ የማለዳ ታይምስ የሚገኝበት ሲሆን ከብሎጎች ደግሞ አቤቶክቻው እና የቅዳሜ ማስታዎሻ የተሰኙት ይገኙበታል። በዛሬው እለት ለንባብ የበቃው የአቤ ቶክቻው ወግ “አንዱ ሲዘጋ በአንዱ እንሾልካልን” በማለት አዲስ ብሎግ ፈጥሮ በመስራት ላይ የሚገኝ መሆኑን የገለጠ ሲሆን ፤በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ተስፋዬ ገብረአብ “ወያኔ ተጨናንቆአል?” ብሎአል ።
በተለይም ደራሲ ተስፋዬ “ርግጥ ነው ሰሞኑን ወያኔ በጣም ተጨናንቆአል። ለአመፅ እርሾ ሊሆኑ በሚችሉ ቁጣዎች ተከበዋል። የሶማሊያ ተልእኮ እየከሸፈ ነው። አልሸባብ እያሸመቀ ደጋግሞ አደጋ መጣሉን በመቀጠሉ፣ ከዚህ በላይ ሶማሊያ መቆየት እንደማይችሉ ተረድተው ጓዛቸውን መሸከፍ ይዘዋል።ከኤርትራ ጋር የጀመሩት የጦርነት ድራማ፣ ላይ ላዩን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ እንደሚያውሉት አለመሆኑ ተባኖበታል። የውስጥ ቀውሱ ተባብሶአል። የመምህራን አመፅ ወዴት እንደሚያመራ አልታወቀም።ቢታፈንም መልኩን ቀይሮ መከሰቱ የማይቀር ነው። የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ነባር ቅርሶች የማውደሙ ሴራ አማኙን ህዝብ ያሸማቀቀና ያስደነገጠ ሆኖአል። ገና አልተቋጨም። ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉት አማሮች ጉዳይ፣ ሊታፈን ባለመቻሉ ፈንድቶ ወጥቶአል። የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱንም ሊቆጣጠሩት አልቻሉም። ሙስናው ጣራ ነክቶአል። ስርቆቱ፣ “ተከተል አለቃህን” የሚል ስያሜ አጊኝቷል። የህወሃት ወገኖች የቅንጦት
ህይወት ይሉኝታ አጥቶአል። እና በዙሪያቸው ያለውን የተቆጣ የህዝብ አይን ለማፈን መጨነቃቸውን ማስተዋል ይቻላል።አፈና ግን መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ምርጫው አንድ ብቻ ነው። ከራስ ጋር እና ከእውነታው ጋር መታረቅ! ሲኢለ ጽፎአል።
የታገዱ ዌብሳይቶችን ለማየት http://www.unblocked.org/ በመግባት እና የዌብሳይቱን ስም በመጻፍ ለመመልከት እንደሚቻል የማለዳ ታይምስ ዌብሳት አዘጋጅ የሆነው ዘላለም ገብሬ የላከልን ዘገባ ያመለክታል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide