መስከረም ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው ባለፈው ታህሳስ ወር 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዳላር ከግል ባንኮች የተበደረው መንግስት፣ ተጨማሪ በድር ለመውሰድ እንቅስቃሴ ጀምሯል።
በሚቀጥለው ሳምንት የመንግስት ባለስልጣኖች ከአበዳሪ ተቋማት መሪዎች ጋር ለንደን ውስጥ ይገናኛሉ። ላዛርድ የተባለ የመንግስት የገንዘብ አማካሪ ድርጅት ባለስልጣኖቹን ከጀርመኑ ዶች ባንክና ከአሜሪካው ጄፒ ሞርጋን ሃላፊዎች ጋር እንደሚያገናኛው የዘገበው ፋይናንሻል ታይምስ፣ ድርድሩ ከተሳካ አገሪቱ ከዚህ ቀደም ከተበደረችው 1 ቢሊዮን ዶላር በተጨማሪ በ10 አመታት ውስጥ በ6 ነጥብ 6 በመቶ ወለድ የሚከፈልበት ብድር ትወስዳለች።
የውጭ ኢንቨስትመንት እና አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልከው የምርት መጠን መቀነሱን ተከትሎ አገሪቱ የገባችበትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመሸፈን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስፍልገውን የብድር አይነት ለመውሰድ ሳትገደድ እንደማትቀር መረጃዎች ያሳያሉ። ገዢው ፓርቲ ከቻይና እና ከሌሎች አለማቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ከ17 እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መበደሩን መረጃዎች ያሳያሉ።