ሚያዝያ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው አቶ ቀናው ክንዴ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ሚያዚያ 6/2007 ዓም ከጧቱ ሁለት ሰአት ላይ የብአዴን ኢህአዴግን የምርጫ ምልክት ቀደዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ግለሰቡ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ በመሆናቸው ብቻ የሃሰት ክስ እንደተመሰረተባቸው ቢናገሩም የጎንደር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በማግስቱ ሚያዚያ 7/2007 ዓም በዋለው ችሎት ግለሰቡ በአንድ አመት እስር እና በሁለት አመት ገደብ እንዲቀጡ ወስኗል።
ፍርድ ቤቱ የሰጠው ፈጣን ውሳኔ ጉዳዩ ፖለቲካዊ መሆኑን ለግለሰቡ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ተናግረዋል።