የኢህአዴግን የልማት ስኬት እንዲመሰክሩ የተጠሩ ሰዎች ያልተጠበቁ ችግሮችን አነሱ

ሰኔ ፮(ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመጪው ምርጫ ለአሸናፊነት ያበቃኛል በማለት ኢህአዴግ በተለያዩ አካባቢዎች  የተመረጡ ሰዎች በአምስት አመታት ውስጥ ስለተሰሩ ስራዎች  እንዲመሰክሩ በማድረግ ላይ ቢሆንም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያልተጠበቁ አስተያየቶችን እያስተናገደ ነው።

በደብረብርሃን ሰሞኑን ተካሂዶ በነበረው ውይይት ህዝቡ የተለያዩ የማህበራዊ አግልግሎት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አንስቷል። ርዕሰ መምህር ከፈለኝ ዘውዴ እንደተናገሩት በከተማዋ ውስጥ ከ15 ሺ ያላነሱ ነዋሪዎች ለ7 ዓመታት መብራት ሳያገኙ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አቶ አባይነህ የተባሉ ነዋሪም እንዲሁ በከተማው ውስጥ የሚታየውን የመብራት እና የስልክ አገልግሎት ችግሮችን አንስተዋል ተስፋየ ዘነበ የተባለ ነዋሪ ደግሞ የከተማው ወጣት በልማቱ ተጠቃሚ አለመሆኑን ገልጿል ወርቁ ገብረኪዳን የተባለ ሰው ደግሞ የጨለማው ሰፈር በሚባል ቦታ እንደሚኖሩ ገልጸው መብራት ካጡ 8 ዓመታት መቆጠሩን ተናግረዋል።

አቶ ወርቁ በከተማቸው የሚታየውን የኑሮ ውድነት አንስተው  መልካም አስተዳደር አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም ብለዋል በህዝቡ አስተያየት የተደናገጡት የኢህአዴግ ሹሞች ለደጋፊዎቻቸው ድል ያለ ግብዣ ሲያዘጋጁ ነቀፌታ ሲያሰሙ የዋሉትን ከግብዣው አግልለዋቸዋል።

ኢህአዴግ ምርጫ 2007ትን አስታኮ የህዝብ ድጋፍ ያስገኛሉ የሚላቸውን እርምጃዎች ሁሉ እየወሰደ ነው።