ኢሳት (ጥር 22 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ከተማ የተሰባሰቡ የአፍሪካ መሪዎች በሶማሊያ ተሰማቶ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል በቀጣዮቹ ሶስት አመታት ተጠቃሎ በሚወጣበት ጉዳይ ዙሪያ መምከር መጀመራቸው ታወቀ።
የሰላም አስከባሪው አጋጥሞት ያለው የገንዘብ እጥረት የወታደራዊ ቁሳቁሶች፣ ያልተቀናጀ አመራር እንዲሁም የአወታደሮች ሞራል ማነስ በሰላም አስከባሪ ሃይሉ ላይ ተፅዕኖን እያሳደሩ እንደሚገኝ በውይይት መነሳቱን ዘ ኢስት አፍሪካ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ማላዊ ኬኒያና ጅቡቲ የተውጣጡ ወደ 22 ሺ አካባቢ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በሶማሊያ የሚገኙ ሲሆን፣ ልዑኩ የሚፈለገውን ያህል ውጤት አላመጣም ተብሎ ከተለያዩ አካላት ዘንድ ትችት እየቀረበበት ይገኛል።
የአውሮፓ ህብረት ለሰላም አስከባሪ ሃይሉ የሚሰጠውን ድጋፍ መቀነስ ተከትሎ ብሩንዲ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ ወታደሮቻቸውን ከወዲሁ ለማስወጣት እቅድ እንዳላቸው ባለፈው አመት ይፋ አድርገዋል።
የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ ያጋጠመውን የበጀት ጉድለት ለማሟላት ከተለያዩ ሃገራት ጋር ድርድር እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን፣ የአውሮፓ ህብረት በየአመቱ ሲሰጥ የነበረው 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በ20 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉ ተመልክቷል።
በጀቱት ባለፈው አመት የቀነሰው የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ህብረት ጋር የደረሰው የድጋፍ ስምምነት በቀጣዩ ወር የሚያበቃ በመሆኑ የሰላም አስከባሪ ሃይሉ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ጋዜጣው የተለያዩ አካላት ዋቢ በማድረግ በዘገባው አስነብቧል።
የልዑኩ ሃላፊ የሆኑት ፍራንሲስኮ ሜዴሪ’ያ (Francisco Maderia) ከቀጣዩ አመት ወር ጀምሮ የተወሰኑ ሰላም አስከባሪዎች ከሶማሊያ መውጣት እንደሚጀምሩ ለዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ አስረድተዋል።
የሰላም አስከባሪ ሃይሉ መውጣት ከጀመሩ በፊት ግን በአልሸባብ ታጣቂ ሃይል ስር ያሉ አካባቢዎች ነጻ ለማስወጣት ጥረት እንደሚደረግ ሃላፊው አክለው ገልጸዋል። በአዲስ አበባ የተሰባሰቡ የአፍሪካ መሪዎች በነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።
በሶማሊያ የሚገኙት የህብረቱ የሰላም አስከባሪ ታጣቂ ሃይሉን ከያዛቸው ይዞታቸው ለማስወጣት ለአመታት ጥረትን ቢያደርጉም ወታደራዊ ዘመቻው የታሰበውን ውጤት አለማምጣቱም ይነገራል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ አልሸባብ በመዲናይቱ ሞቃዲሾ ከተማ ጨምሮ በተለያዩ ግዛቶች እያደረሰ ያለው ጥቃት መጨመሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ታጣቂ ሃይሉ ከቀናት በፊት በአንድ የኬንያ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ በፈጸመው ጥቃት በርካታ ወታደሮች መሞታቸው ይታወሳል።
የኬንያ መከላከያ ሰራዊት ኩልቢዮ ተብሎ በሚጠራ የኬንያና ሶማሊያ ድንበር አካባቢ በተፈጸመው ጥቃት ዘጠኝ የኬንያ ወታደሮች እንደሞቱ መረጋገጡን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሰራዊቱ ቃል አቀባይ የሆኑት ሌተናል ኮሎኔል ፖል ጅኑጉና ወደ 70 የሚጠጉ የአልሸባብ ታጣቂዎች በጥቃቱ መገደላቸውን አስታውቋል።
ባለፈው አመት ታጣቂ ሃይል በአንድ የኬንያ ወታደራዊ ይዞታ ላይ በፈጸመው ተመሳሳይ ጥቃት ከ100 የሚበልጡ የኬንያ ወታደሮች መሞታቸው ይታወሳል።