ጥቅምት ፳፱(ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮምሽን በመካሄድ ላይ ባለው 6ኛው የአፍሪካ ሚዲያ አመራሮች
ፎረም ላይ ኢህአዴግ የሚያቀነቅነው የልማታዊ ጋዜጠኝነት ጽንሰ-ሀሳብ በአፍሪካ ጋዜጠኞች ተተችቶአል። ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች ችግሮቻቸውን ፊትለፊት አውጥተው መናገር ባለመቻላቸውም ወቀሳ ደርሶባቸዋል።
ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ በዚሁ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የፕሬስ ነጻነት በኢትዮጽያ መረጋገጡን በማውሳት ፕሬሱ ግን በውስጡ የአቅም ውስንነቶች እንዳሉበት ይህን ችግር ለመፍታት መንግታቸው እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ኃ/ማርያም በንግግራቸው አገሪቱ የፕሬስ ነጻነት አክባሪ መሆንዋን ከመናገር ውጪ በመንግስታቸው ውስጥ ያሉ የፕሬስ ማነቆዎችን ሳያነሱ አልፈውታል፡፡በጉባዔው ላይ ከደቡብ አፍሪካ ተጋብዘው የመጡ አንድ ተሳታፊ
በኢትዮጵያ ከ70 በላይ ፕሬሶች ባለፉት ዓመታት በመንግስት ጫና መዘጋታቸውን፣ ሰባት ያህል ጋዜጠኞች በሸብርተኝነት ተከስሰው በእስር ላይ እንደሚገኙ መረጃ እንዳላቸው በመጥቀስ የኢትዮጵያን መንግስት ተችተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ሌላ ተሳታፊ የጉባዔው መሪ ቃል አፍሪካ ትናገር እንደሚል በማስታወስ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችን ስለችግራቸው ለምንድነው የማይናገሩት በሚል ጠይቀዋል፡፡ ይህ ያለመናገራቸው ሁኔታ በእርግጥም ችግር መኖሩን
እንደሚጠቁም ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሃሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ በሸብርተኛነት ተከስሰው በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች መኖራቸውን በመጥቀስ ጉባዔው በዚህ ጉዳይ ላይ በግልጽ እንዲወያይና አቁዋሙን ሊገልጽ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የኮምኒኬሽን ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ የፕሬስ መብት ረጋጭ አገር ሆና እንዲህ ዓይነት አህጉራዊ ጉባዔ ልታዘጋጅ አይገባትም በሚል ከአንዳንድ ወገኖች የቀረበውን ትችት በተመለከተ ተጠይቀው እነዚህ ወገኖች
የኢትዮጽያን ተጨባጭ ሁኔታ የማያውቁ እና ጸረ ልማት ሃይሎች ናቸው በማለት የተለመደ የማጣጣል ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ጉባዔው ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን ማምሻውን የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር እና የኬንያው አቻቸው በተገኙበት የማጠቃለያ ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ተጨማሪ የአፍሪካ ሚዲያ ሊደርስ ፎረም በዛሬው ዕለት መካሄዱን የቀጠለ ሲሆን ዛሬ ኢትዮጵያዊያን በፕሬስ ጉዳይ አፈና መኖሩን ይፋ አድርገዋል፡፡ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን፣ በርካታዎች መሰደዳቸውን በመጥቀስ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ከሚሰደዱባት አገራት በሶስተኛ ደረጃ እንደምትገኝ አንድ ተሳታፊ ገልጸው የፕሬስ አፋኝነቱ የታወቀ ነው ብሎአል፡፡
የመንግስት ካድሬዎች በአዳራሹ ውስጥ በብዛት ቢኖሩም ብዙዎቹ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሃሳባቸውን መግለጽ በመፍራት ሳይናገሩ ቀርተዋል፡፡ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ይገኛሉ የተባሉት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሳይገኙ ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን ተገኝተዋል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ ልማታዊ ዘገባን በማፋጠን የአፍሪካን መንግስታት ማገዝ ወሳኝ ጉዳይ ነው በሚል በኢህአዴግ የቀረበው የመወያያ ሀሳብ ጋዜጠኞች ሳይቀበሉት ቀርቷል።
ጋዜጠኞቹ ” ችግር ካልዘገብን ምኑን እንዘግባለን ” ያሉ ሲሆን፣ መንግስትን የምንረዳው ኢትዮጵያ እንዳቀረበችው ልማታዊ ጋዜጠንነት ሳይሆን፣ የምርመራ ጋዜጠኝነት በመስራት ነው ብለዋል።
ልማታዊ ጋዜጠኝነት የህዝብ ግንኙነት ወይም የልማት ኮሚኒኬሽን ስራ ነው ያሉት ጋዜጠኞች፣ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ሙያን ያጠፋል ፣ ጋዜጠኛውን ከጋዜጠኝነት አውጥቶ የህዝብ ግንኙነት ሰራተኛ ያደርገዋል በማለት ተቃውመዋል። በመንግስት የቀረበውን ሀሳብ ከሞዛምቢክ ከመጡ ጋዜጠኞች በስተቀር ሁሉም ውድቅ አድርገውታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድነት ፓርቲ ባወጣው መግለጫ በርካታ የአፍሪካ ሚዲያ ባለሙያዎች የፕሬስ ነፃነት ባልተረጋገጠበት፣ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ተልካሻ ሰበብ እየተፈለገ በሚዘጉበት፣ ጋዜጠኞች ሀገር ጥለው እንዲሰዱ በሚደረግበት፣ በሀገር ውስጥ አንድም የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ባልተቋቋመበት፣ ስርዓቱን የሚተቹ ጋዜጠኞች ወደ እስር የሚወረወሩበትና የሚታሰሩበት ገዥ ስርዓት ባላት አገር መዘጋጀቱ ላይ ተቃውሞ ባይኖረንም፣ ጉባኤው በገዥዎች የሚጨቆነው የአፍሪካ ሚዲያ ላይ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ የለንም ሲል አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡
የአፍሪካ የሚዲያ ባለሙያዎች የሚዲያ ነፃነት የሚረጋገጠው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲረጋገጥ መሆኑን አምነው በቅድሚያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይገነባ አንቀው በመያዝ የህዝቡንና የሚዲያውን ነፃነት ጨፍላቂ የሆኑትን አምባገነን ስርዓቶች መታገል እንደሚገባ የገለጸው አንድነት፣ በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥም ነፃ ሚዲያ መመስረት አይታስብም ሲል አክሎአል።
ኢህአዴግ ስርአት ለነፃ ሚዲያ ማበብ ቁርጠኝነት ያነሰው በመሆኑ ከማስመሰል ባለፈና ለስርዓቱ አጨብጫቢ የሆኑ ሚዲያዎችን ከመቀፍቀፍ በዘለለ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ መጎልበት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ተች ሚዲያዎችን ሊፈጥር አለመቻሉን አውስቷል።
በኢትዮጵያችን ያለው አምባገነን ስርዓት በርካታ ጋዜጠኞችን እስር ቤት ማጎሩን፣ ጠንካራ የግል ጋዜጦችንም መዝጋቱን፣ ፓርቲው ጠቅሶ፣ በሀገራችን ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ ብቻ ለእስር የተዳረጉት አንዲፈቱና የሚዲያ ባለሙዎችም ይህንን በአካል ቃሊቲ በመሄድ ከእስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ የሱፍ ጌታቸውና ዝዋይ የሚገኘውን ውብሸት ታየን በማነጋገር እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርቧል።