ኢሳት (ጥቅምት 24 ፥ 2009)
በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ውስጥ በቅርቡ ውክልናን ያገኘው የአውሮፓ ህብረት የአህጉሪቱ አባል ሃገራት በጋዜጠኞች ላይ የሚወስዱትን አፈናና ግድያ እንዲያቆሙ አሳሰበ።
በአፍሪካ ህብረት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ልዩ ጥበቃና ከለላ እንደሚደረግለት ቢደነገግም አሁንም ድረስ የጋዜጠኞች እስራትና ወከባ እንዲሁም አፈና ሊቆም አለመቻሉን የአውሮፓ ህብረት ከአዲስ አበባ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በጋዜጠኞች ላይ ወከባን እየፈጸሙ ያሉ ሃገራት ከድርጊታቸው መታቀብ ለአህጉራዊና ለአለም አቀፍ ደንቦች ተገዢ እንዲሆኑ ድርጅቱ ጥሪውን አቅርቧል።
በጋዜጠኞች ላይ ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ የመንግስትና ሌሎች ተቋማት ገለልተኛ ማጣራት ተካሄዶባቸው ለፍትህ መቅረብ ይኖርባቸዋል ሲል ከ10 የሚበልጡ ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገው በሚገኙበት አዲስ አበባ የሚገኘው ህብረቱ በመግለጫው አስፍሯል።
በጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ያለው ይኸው ወከባና እንግልት የሚቀርበትን መንገድ ለማበጀት የአውሮፓ ህብረት ከአንድ ሳምንት በኋላ ለሁለት ቀን የሚቆይ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱም ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት የጋዜጠኞችን መብት ለማስጠበቅ ይረዳል ያለውን የውሳኔ ሃሳብ በቅርቡ ማስተላለፍ ይታወሳል።
ለዚሁ የውሳኔ ሃሳብ ድጋፍን የገለጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በአህጉሪቱ ያሉ ጋዜጠኞችን መብት እንዲያስጠብቅም አክሎ አሳስቧል።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ኮሜቴ ቱ ፕሮቴክት ጆዎርናሊስት (CPJ) ኢትዮጵያ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ከአህጉሪቱ ግንባር ቀደም መሆኗን በአለም አፋኝ ከተባሉ 10 አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ይገልጻል።