ጥር ፳፮ (ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአፍሪካ አገራት 28ኛው የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ የኅብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ሰሞኑን ሲካሄድ ሰንብቷል። ከስብሰባው መቃረቢያ ሰሞን ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ የከተማ ነዋሪዎች በፀጥታ ሃይሎች ከመጠን ያለፈ ቁጥጥር ምክንያት የሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ የእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ለከፍተኛ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ተዳርገዋል።
በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ በሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች አቅራቢያ ላይ መኪና ማቆም፣ ሰዓት እላፊ የተጣለ በሚመስል መልኩ በምሽት የመዘዋወር መብታቸው ተገድቧል። ይህን ያልታወጀ ገደብ ሳይረዱ በምሽት ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ዜጎች በፀጥታ ሃይሎች ድብደባ፣ እስራትን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች ተፈጽሞባቸዋል። በተለይም በአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤት አቅራቢያ በሚገኙ በቦሌ እና አካባቢዋ ያሉ ነዋሪዎችና የንግድ ድርጅቶች፣ የምሽት መዝናኛዎች፣ የገበያ ማዕከላት በደኅንነቶች ሲዋከቡ ሰንብተዋል። ከእንቅስቃሴ ውጪ በመሆናቸው ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ኤኮኖሚያዊ ኪሳራ ደርሶባቸዋል። የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ ነዋሪዎቹ ወደ መደበኛ እለታዊ እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸው እፎይታ እንደሰጣቸው ምንጮቻችን ገልፀዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን በመቃወም በኢትዮጵያ ያለው የመብት ጥሰቶች እየተባባባሱ መቀጠላቸውን በመጥቀስ ”ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባን ለማስተናገድ የድኅንነት ዋስትና ችግር አለባት” ሲሉ ተሰናባቿ የቀድሞዋ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል። የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የኅብረቱ ፕሬዚዳንት ያቀረቡትን ወቀሳ ተከትሎ የህወሃት ኢህአዴግ የፀጥታ እና የደኅንነት ሃይሎች ጉባዔውን በስኬት ለማጠናቀቅ ሲሉ የከተማዋን ነዋሪዎች መብት በመጨፍለቅ ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰቶችን በከፋ ሁኔታ ሲፈጽሙ ሰንብተዋል።
በ28ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባኤ ላይ ሶስት አንኳር ክስተቶች ተከስተዋል። የቻድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሳ ፋቂ መሃማት ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማን ተክተው ባልተጠበቀ ሁኔታ ተፎካካሪያቸውን የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር አሚና መሀመድ በማሸነፍ የኅብረቱ አዲስ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። ሞሮኮ ከ53 የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ውስጥ በ39 የድጋፍ ፣ በአስር ድምጸ ተአቅቦ ከ33 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ኅብረት አባልነት ተመልሳለች። የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባልነት ለመውጣት ውሳኔ ያሳለፉ ሲሆን ሴኔጋል እና ናይጄሪያ ይህን ውሳኔ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውመዋል። መቀመጫውን በኔዘርላንድ ዘሄግ ያደረገው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ እንዲመሰረት 34 የአፍሪካ አገራት ትብብር አድርገዋል።
በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በተጋባዥነት ተገኝተዋል። የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ”በምስራቅ አፍሪካ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ተጠቂ ለሆኑ አገራት በተለይም በኢትዮጵያ ለተከሰተው የርሃብ አደጋ አፋጣኝ የሆነ ረድኤት በማቅረብ የርሃብ ተጠቂዎችን ሕይወት መታደግ አለብን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።