የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጸሃፊ የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ ለሚታየው ችግር አስቸካይ መፍትሄ እንዲፈልግ ጠየቁ

ጥቅምት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የአፍሪካ ሕብረት ዋና ጸሃፊ የሆኑት ኒኮላ ዛና ዲላሚኒ ዙማ በኢትዮጵያ የተነሳውን ሕዝባዊ አመጽ አስመልክቶ ሁሉን ያሳተፈ አስቸኳይ የሆነ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርብዋል። ዋና ጸሃፊዋ ሁሉንም ያሳተፈ ድርድር ማድረግ ለአገሪቷ የመጨረሻ አስተማማኝ እና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ያስገኝላታል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ምክንያት በማድረግ መሰረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶችን እንዳይጥስም አሳስበዋል። መንግስት የዘጋውን የኢንተርኔት አገልግሎት ካለምን ቅድመ ሁኔታዎች በመክፈት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ አለበት ሲሉ ዋና ጸሃፊዋ ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ከዚህ ቀደም ጠንካራ ትችት አቅርቦ አያውቅም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ በሁዋላ፣ ህብረቱ በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ላይ ትችት መሰንዘር ጀምሯል።