የአፍሪካ ስፖርት ፌዴሬሽን ካፍ ኢትዮጵያን 10 000 የአሜሪካ ዶላር መቅጣቱን አስታወቀ

ጥር ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአፍሪካ ስፖርት ፌዴሬሽን ካፍ ኢትዮጵያን 10 000 የአሜሪካ ዶላር መቅጣቱን አስታወቀ:: ሳላሀዲን ሰኢድ ከዛምቢያ ጋር በተደረገው የመጀመሪያ ግጥሚያ ምርጥ ተጫዋች ተባለ::

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ባደረገው ግጥሚያ ደጋፊው ህዝብ የተለያዩ ነገሮችን ወደ ሜዳው በመወርወር በዛምቢያ ቡድን ላይ ላሳየው ተቀባይነት የሌለው ተቃውሞ ቅጣቱ መጣሉን ቢቢሲ አመልክቶል::

በደቡብ አፍሪካ ቅዳሜ እለት በሁለቱ ቡድኖች መካከል በተደረገው ጨዋታ በረኛው ጀማል ጣሰው በቀይ እንዲወጣ ዳኛው ከወሰኑ በሆላ ነበር በስታዲየሙ የሚገኘው ደጋፊ የተለያዩ ነገሮችን ወደ ኮስ ሜዳው በመወርወር ቁጣውን የገለጠው::

በዚህ የተነሳ ካፍ በኢትዮጵያ ላይ 10 000 የአሜሪካ ዶላር ቅጣት የወሰነ ሲሆን ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ጥፋት ላይ ባለመገኝቶ የቅጣቱ ግማሽ እንደሚነሳላት ከቢቢሲ ዘገባ ለመረዳት ተችሎል::

በረኛው ጀማል ጣሰው በካፍ ህግ መሰረት ከዛምቢያ ጋር የተደረውን ጨዋታ ጨምሮ በሁለት ጨዋታዎች እንዳይሳተፍ መቀጣቱ ይታወቃል::

ይህ በዚ ሳለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዛምቢያ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ ሳላሀዲን ሰኢድ የጨዋታው ኮከብ ተሰኝቶ የኦሬንጅ ካፕ ተሸላሚ ሆኖል::

በአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በየግጥሚያው ምርጥ ተጨዋች ተመርጦ የኦሬንጅ ካፕ ተሸላሚ የሚሆን ሲሆን ሳላሀዲን ሰኢድም ይህንኑ ሽልማት ነው ያገኘው::