የአፍሪካ ህብረት 29ኛው የመሪዎች ጉባኤ የአህጉራዊውን ተቋም የፋይናንስ ምንጭ በራሱ ለመሸፈን በሚያስችሉና አሰራሩን ለማጎልበት በሚያበቁ ጉዳዮች ለመምከር በአዲስ አበባ ሰኞ ተጀመረ ።
ህብረቱ ለሁለት ቀናት በሚያካሂደው ጉባኤ በአህጉሪቱ የጸጥታና የሰላም ጉዳዮች ላይም እንደሚመክር ዘገባዎች አመልክተዋል ።
የአፍሪካ ህብረት እስካሁን በነበረው ሁኔታ ወጪዎቹ የሚደጎሙት ከአውሮፓ ህብረትና ከተለያዩ እርዳታ ሰጪዎች በሚለገሰው ገንዘብ ነው ። ከዚህ በተጨማሪም የህብረቱ ሃገራት የሚያዋጡት የአባልነት መዋጮ ገንዘብም የአህጉራዊ ተቋሙ የስራ ማካሄጃ በመሆን ሲያገለግል ቆይቷል ።
የተወሰኑ አባል ሃገራት መዋጮአቸውን በአግባቡ የማይከፍሉ በመሆናቸው ግን የአፍሪካ ህብረት የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥመው እንደ አውሮፓ ህብረት ያሉ ተቋማት ሲደጉሙት ነበር ።
አሁን ግን የኣአፍሪካ ህብረት ወጭውን በራሱ ለመሸፈን በሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ የተዘጋጀ የማሻሻያ ሰነድ ቀርቦ በአሁኑ የመሪዎች ጉባኤ ውይይት እንደሚደረግበት ተገልጿል።
የመሪዎቹ ጉባኤ በጸጥታ ጉዳይ ላይ በሚያደርገው ውይይትም በተለይም በደቡብ ሱዳን ፣በሶማሊያ፣ በሊቢያ እንዲሁም በማእከላዊ አፍሪካ ባሉ ግጭቶች ጉዳይ ላይ እንደሚመክርም ለማወቅ ተችሏል ።
በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው በኤርትራና ጅቡቲ መካከል ያለው ውጥረትም የጉባኤው አጀንዳ መሆኑም ተዘግቧል ።
የቻድ ዜግነት ያላቸው የአፍሪካ ህብረት አዲሱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጉባኤው ከተጠቀሱት በተጨማሪ በአህጉሪቱ የጸጥታ ችግር ባለባቸው ሌሎች ሃገራትም ምክክር እንደሚያደርግም ገልጸዋል ።
በመሪዎቹ ጉባኤ መክፈቻ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር አልፋ ኮንዴ አፍሪካ ያሏትን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም ለወጣቱ ትኩረት እንድትሰጥ ጠይቀዋል።