ኢሳት (ሃምሌ 14 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ ወታደሮች በቅርቡ 14 ሰላማዊ ሰዎችን በሶማሊያ ገድለዋል የተባለውን መረጃ ምርመራ ሊያካሄድበት መሆኑን በሃገሪቱ በሰላም ማስከበር ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ልዑክ ይፋ አደረገ።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ባለፈው ሳምንት በቤይ ግዛት በምትገኘው የዋርዲንግ ከተማ አካባቢ ከአልሸባብ ታጣቂ ሃይል ጋር ውጊያን ባካሄዱ ጊዜ በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል የሚል መረጃ እንደደረሰው ልዑኩ መገልጹን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
የአይን እማኞች ኢትዮጵያውያኑ ወታደሮች በጸሎት ስነስርዓት ላይ የተኩስ እርምጃን በመውሰድ በትንሹ 14 ንጹሃን ሰዎች እንደገደሉ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጻቸው ይታወሳል።
የመረጃው መሰራጨትና የቀረበለትን አቤቱታ ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ድርጊቱን ፈጽመዋል በተባሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ምርመራን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ልዑኩ የሚካሄደው ይኸው ምርመራ እንደተጠናቀቀ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ሲል የሰላም አስከባሪ ልዑኩ አክሎ አመልክቷል።
ከተገደሉት 14 ሰዎች መካከል አንጋፋ የሃገር ሽማግሌዎች እንደሚገኙበት እና ድርጊቱ በአካባቢው ቁጣ ማስነሳቱ ኢብራሂም ኢሳክ ያሮው የተባሉ የፓርላማ አባል ለዜና አውታሩ ተናግረዋል።
የሰላም አስካባሪ ልዑኩ ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ ምርመራ ለማካሄድ መወሰኑን ቢገልጽም የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው ምላሽ የለም።
ወደ 5ሺ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ልዑክ ስር እያገለገሉ የሚገኝ ሲሆን፣ ተጨማሪ ቁጥሩ ያልታወቀ የሰራዊት ቡድንም የተናጠል ውጊያን ለማካሄድ በሶማሊያ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ይኸው በሶማሊያ በተለያዩ ግዛቶች ተሰማርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ የሰራዊት አባላት ከአልሻባብ ታጣቂ ሃይል ጋር ውጊያን እያካሄደ እንደሚገኝ የሶማሊያ ባለስልጣናት ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያያን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት የተውጣቱ ወደ 20ሺ አካባቢ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በሶማሊያ ቢገኙም ታጣቂ ሃይሉ አልሻባብ አሁንም ድረስ የሃገሪቱ ስጋት ሆኖ መቀጠሉ ይነገራል።