የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ከአለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጅምላ እንዲወጡ ያስተላለፈው ጥሪ ተቃውሞ ገጠመው

ኢሳት (ጥር 24 ፥ 2009)

የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት ከአለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጅምላ እንዲወጡ ያስተላለፈው ጥሪ ተቃውሞን ቀሰቀሰ።

ትላንት ማክሰኞ ለሁለት ቀን ሲያካሄድ የቆየውን የመሪዎች ጉባዔ ያጠናቀቀው ህብረቱ ወደ 34 አካባቢ የሚጠጉ የአፍሪካ የፍርድ ቤቱ አባላት በጅምላ እንዲሰናበቱ መጠየቁን ቢቢሲ ዘግቧል። ይሁንና፣ ናይጀሪያና ሴኔጋል ህብረቱ ያቀረበውን ጥሪ አጥብቀው ኮንነዋል።

በርካታ የአፍሪካ ሃገራት የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የአፍሪካ መሪዎችን ኢላማ አድርጎ ይሰራል ሲሉ ተቃውሞን ሲያቀርቡ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

ይሁንና የአለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ በአፍሪካ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ፍትህ እንዲያገኙ ከማድረግ ውጭ ፍትሃዊ ያልሆነ ነገር ሰርቷል መባሉን እንዳስተባበለ ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።

ከ34ቱ የአፍሪካ የፍርድ ቤቱ አባል ሃገራት መካከል ደቡብ አፍሪካና ብሩንዲ መንግስታት ከአባልነት ለመውጣት ከወራት በፊት ውሳኔን አስተላልፈው እንደነበር አይዘነጋም።

ከተወሰኑ አባል ሃገራት የቀረበን ጥያቄ ተከትሎ የአፍሪካ የመሪዎች ልዩ ጉባኤ ትናንት ማከሰኞ በጉዳዩ ዙሪያ ሰፊ ውይይትን ያካሄደ ሲሆን በማጠቃለያም የህብረቱ አባል ሃገራት ከፍርድ ቤቱ አባልነት በጅምላ እንዲወጡ ጥሪን አቅርቧል። የህብረቱ ውሳኔ ግን አስገዳጅ አለመሆኑ ተነግሯል።

በጉዳዩ ዙሪያ ምክክርን ያካሄዱ የአፍሪካ መሪዎች ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመወያየት ፍርድ ቤቱ ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥረት እንዲያደርግ ሃሳብ ማቅረባቸውንን ለመረዳት ተችሏል።

የሱዳኑ ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር በሃገራቸው የዳርፉር ግዛት ፈጽመውታል በተባለ የጦር ወንጀል በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከአመታት በፊት የእስር ትዕዛዝ እንደተላለፈባቸው የሚታወስ ነው።

በአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ፕሬዚደንት አል በሽር ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈባቸውን ውሳኔ በመቃወም የፈጸሙት የጦር ወንጀል እንደሌለ አስተባብለዋል። ይሁንና ፕሬዚደንቱ ከተላለፈባቸው የእስር ትዕዛዝ ለማምለጥ በአለም አቀፍ ዙሪያ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄን እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የሱዳኑ ፕሬዚደንት ልዩ ያለመከሰስ ዋስትና ተሰጥቷቸው ባለፈው አመት አባል ሃገር በሆነችው ደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ጉብኝት በደቡብ አፍሪካ የህግ ጥያቄን አስነስቶ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው የአፍሪካ መሪዎች ከፍርድ ቤቱ ለመውጣት የያዙትን አቋም ለሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ተጠያቂ ላለመሆን ነው በማለት ዕርምጃውን እየተቃወሙት ይገኛል።

123 የአለም ሃገራት በአባልነት የሚገኙበት ፍርድ ቤቱ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2002 አም የተቋቋመ ሲሆን፣ የጦር ወንጀልን ጨምሮ የጅምላ እንዲሁም የዘር ማጥፋት ግድያን በመመርመር ተጠያቂዎችን ለፍትህ ለማቅረ እንደሚሰራ መረጃዎች ያመለክታሉ።