ኢሳት (ሃምሌ 6 ፥ 2008)
ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከ20 ሺ በላይ የሰላም አስከባሪ ሀይል በሶማሊያ አሰማርቶ የሚገኘዉ የአፍሪካ ህብረት በቀጣዮቹ አራት አመታት ከሶማሊያ ጠቅልሎ እንደሚወጣ ይፋ አደረገ።
በጉዳዩ ዙሪያ ሰሞኑን ልዩ ጉባዔን ያካሄደዉ የህብረቱ የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት ከቀጣዩ ሁለት አመታት ጀምሮ የፀጥታና የደህንነት ሀላፊነቶች ለሱማሊያ እንዲተላለፍ ውሳኔ መድረሱን እንደገለፀ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የአውሮፓ ህብረት ለሰላም አስከባሪዉ ሀይሉ ሲሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲቀንስ ያስተላለፈዉን ዉሳኔ ተከትሎ ዩጋንዳ ወደ 6 ሺ አከባቢ የሚጠጋ የሰላም አስከባሪ ሀይሏን ከሱማሊያ እንደምታስወጣ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
የዩጋንዳዉ ፐሬዘደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የሰላም ልዑኩ ካጋጠመዉ የገንዘብ እጥረት በተጨማሪ የሰላም አስከባሪዉ ሀይሉ በትክክለኛ አቅጣጫ ባለመመራቱ ለ10 አመት ያክል አመርቂ ዉጤት አለመምጣቱን ሰሞኑን ገልፀዋል።
ዩጋንዳ ጦሯን ከሱማሊያ ለማስወጣት የያዘችዉን እቅድ ይፋ ማድረግ ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2018 እስከ 2020 ድረስ የደህንነት ሀላፊነቶችን ለሱማሊያ ለማስረከብ እቅድ መንደፉን አስታዉቋል።
ህብረቱ ከ10 አመታት ቆይታ በኋላ ከሱማሊያ ጠቅልሎ ለመዉጣት ፍላጎቱን ቢገልፅም የሶማሊያ ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የሰጡት ምላሽ የለም።
ኢትዬጵያን ጨምሮ ዩጋንዳ ፣ ኬንያ ፣ ጁቡቲ ፣ ቡሪንዲ ፣ እና ሴራሊዮን የተወጣጡ ወደ 22 ሺ አካባቢ የሰላም አስከባሪዎች በሶማሊያ ተሰማርተዉ እንደሚገኙ ታዉቋል።
ኢትዬጵያ ወደ 5ሺ የሚጠጋ ወታደሮችን በህብረቱ ስር በሰላም አስከባሪነት ብትሰማራም ቁጥሩ ሊታወቅ ያልቻለ ሰራዊትን በተናጥል በሶማሊያ በማሰማራት ከአል-ሸባብ ታጣቂ ሀይል ጋር በዉጊያ ዉስጥ ትገኛለች።
የአፍሪካ ህብረት ሀገሪቱን ለቆ ለመዉጣት የያዘዉን እቅድ ይፋ ቢያደርም ኢትዮጵያ በተናጥል አሰማርታ ስላለችዉ ሰራዊት የሰጠችዉ ምላሽ የለም።
የአዉሮፓ ህብረት በሶማሊያ ተሰማርተዉ ለሚገኙ የሰላም አስከባሪዎች በየሀገራቸዉ ከሚከፈላቸዉ ደሞዝ በተጨማሪ በየወሩ ወደ 1 ሺ 200 ዶላር አከባቢ የኪስ ገንዘብን እየሰጠ እንደሚገኝ በቅርቡ መግለፁ ይታወሳል።