የአፍሪቃ ቀንድ አሁንም ለረሃብና ለምግብ እጥረት የተጋለጠ እንደሆነ ጥናቶች አረጋገጡ

የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአፍሪቃ ቀንድ ቁጥሩ 13 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ የምግብ እጥረት እንዳለበትና በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ለረሃብ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እንዳለ ኦክስፋምና የእንግሊዝ ህፃናት አድን ድርጅት ያወጡት ሪፖርት ገልጿል።

ከ50 እስከ 100 ሺህ ሰዎች እንደሞቱበት በሚነገረዉ በአፍሪቃ ቀንድ ተከስቶ የነበረዉ የረሃብ አደጋ በክፍለ ዘመኑ ከታዩት ሁሉ በአይነቱ ልዩ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ ክስተት እንደነበር ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ድርቅ ባሰከተለዉ ችግር ምክንያት የተፈጠረ አደጋ ቢሆንም የሰዉ ልጅ ድክመት አደጋዉን እንዳባባሰዉ ተገልጿል።

በምስራቅ አፍሪቃ የሚታየዉ የምግብ እጥረት ከመቀጠሉ ጋር በምእራብ አፍሪቃ በመታየት ላይ ያለዉ ሁኔታ የአፍሪቃ የምግብ እጥረት በገጠሩ ህብረተሰብ ላይ ብቻ ያተኮረ ክስተት እንዳልሆነ ሪፖርቱ አስታዉቋል።

በአንድ ወቅት ገበሬና ወዛደር የነበሩና የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ ከተማ የፈለሱ ሁሉ የምግብ እጥረት እየገጠማቸዉ እንደሆነ በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰ በኸፊንግተን ፖስት ላይ ከቀረበዉ ዘገባ ለማወቅ ተችሏል።

ሁለቱ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ እና የኬንያ መንግስታት የተረጅውን ቁጥር ዝቅ አድረገው በመናገራቸው ተጠያቂ መሆናቸውን መግለጣቸው ይታወሳል።