ኢሳት (ሚያዚያ 26 ፥ 2009)
በአፋር ክልል የ33ቱም ወረዳ አመራሮች ለስልጠና መቀሌ ሲገቡ፣ የክልልና የወረዳ አመራሮች ደግሞ አዲስ አበባ መሄዳቸው ታወቀ። የወረዳ አመራሮች በአሳይታና በሰመራ መሰልጠን እየቻሉ ወደ መቀሌ መጓዛቸው በክልሉ ቅሬታ መፍጠሩን ምንጮች ገልጸዋል።
ከአፋር 33ቱ ወረዳዎች ወደ መቀሌ የተጓዙ 600 ያህል አመራሮች ሲሆን፣ በቆይታቸው ወቅት የውሎ አበልም ሆነ፣ ሙሉ ለሙሉ የሆቴል ወጪያቸው የሚሸፈነው በአፋር ክልል መንግስት እንደሆነም ታውቋል። በአፋር ክልል መንግስት ወጪ የሚሰጥ ስልጠና ለምን ከክልሉ ወጥቶ ወደ መቀሌ ሄደ ለሚለው ምላሽ አልገተኘም።
ስልጠናው በሰመራና በአሳይታ ቢካሄድ ከገቢም አንጻር ለክልሉ ሆነ፣ በክልሉ የሚገኙ ሆቴሎች ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር። የሚለው ለተቃውሞ በምክንያትነት እየቀረበ ሲሆን፣ አንዳንድ ወረዳዎች ከመቀሌ በብዙ መቶ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሆነው ሃላፊዎቹ አሳይታና ሰመራን አልፈው መቀሌ ድረስ መጓዛቸው በምክንያትነት እየተጠቀሰ ይገኛል።
በአካባቢው ተወላጆች ዘንድ አፋር ክልል የትግራይን ዞን ይመስል በህወሃት ሰዎች ተፅዕኖ ውስጥ ወድቋል በሚል ቀደም ሲልም ቅሬታ ይቀርብ እንደነበር ማስታወስ ተችሏል።
በክልሉ ኢንቨስትመንት በተለይም በጨው ማምረት ስራ በስፋት ተሰማርተው የሚገኙት የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውም ሲጠቀስ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት የአፋር የዞንና የክልል አመራሮች ወደ አዲስ አበባ የወረዳ አመራሮች ወደ መቀሌ መጓዛቸውን ተከትሎ በክልሉ የአመራር ክፍተት መፈጠሩም ተመልክቷል።