ኢሳት (ጥቅምት 28 ፥ 2009)
የአፋር ህዝብ እየደረሰበት ያለው መከራ ከምንጊዜውም በላይ እየከፋ በመምጣቱ የኦሮሞዎችንና የአማራዎችን እንዲሁም የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ትግል የሚቀላቀልበት ምዕራፍ ላይ መድረሱን ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ ገልጹ።
የአፋር ህዝብ ሱልጣን በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙት የቀድሞ ዲፕሎማትና የክልሉ ፕሬዚደንት ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ፣ በቅርብ ወራት ውስጥ የአፋርን ህዝብ የለውጥ እንቅስቃሴ እናያለን ሲሉ ለኢሳት በሰጡት ቃለ-ምልልስ ተናግረዋል።
ሱልጣን ሃንፍሬ አሊምራህ በዋሽንግተን ዲሲ ኢሳት ስቱዲዮ ተገኝተው በሰጡት ቃለ-ምልልስ ለምና ሃብታም የነበረው የአፋር ክልል ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቁን ገልጸው፣ ድህነቱና ጎስቁልናው እየተባባሰ በመምጣቱ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ የአፋር ለማኝ የሚታይበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ሲሉ ተደምጠዋል።
በንጉስ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ይካሄድባት በነበረው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የአፍሪካ ኩዌት ስትባል የነበረችው የአፋር ዋና ከተማ የነበረችው አሳይታ፣ ዛሬ ፍፁም የተረሳችና አስታዋሽ የሌላት ከተማ ሆና መገኘቷን ሱልጣን ሃፍንፍሬ አሊሚራህ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ ዋና ከተማ ከአሳይታ ወደ ሰመራ እንዲሸጋገር የተፈለገው የአፋር ሱልጣኖች መቀመጫ የሆነችው አሳይታን ከህዝብ ልብና አዕምሮ ውስጥ ለማስወጣትና ባህላዊውን ስርዓት ለማጥፋት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
ከአራት አመታት በፊት የሱልጣን አሊ ሚራህን ማለፍ ተከትሎ፣ የሱልጣን ማዕረጉን የወረሱትና ባዕለ-ሲመታቸው በአፋር ክልል በአሳይታ ያካሄዱት ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ፣ የጅቡቲውን ጠቅላይ ሚኒስቴር ጨምሮ 11 ሚኒስትሮች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ አፋሮች ከኤርትራና ከጅቡቲ በክብረ-በዓሉ ሲገኙ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት አለመሳተፋቸውን፣ ይልቁንም ኢትዮጵያውያን አፋሮች እንዳይገኙ የተለያዩ ተፅዕኖ ማድረጋቸውን እንዲሁም ሂደቱን ለማደናቀፍ 2 ሚሊዮን ብር መመደባቸውን ለኢሳት ዘርዝረዋል።
የደርግ መንግስት ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ከደርግ ጋር የተካሄዱ ድርድሮች ውጤት አልባ በመሆናቸው በሰኔ ወር 1967 ከፍተኛ መስዋዕትነት የጠየቀ ውጊያ ከደርግ ጋር ያካሄደው የአፋር ነጻነት ግንባር፣ ለ17 አመታት በትግል ላይ መቆየቱን ገልጸዋል። ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር፣ የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር መላውን የአፋር ክልል በማስተዳደር እንዲሁም በሽግግግር መንግስት ውስጥ አራት የም/ቤት መቀመጫ ማግኘቱን አስታውሰዋል።
በመላ ኢትዮጵያ በተካሄደው ምርጫ፣ የአፋር ነጻነት ግንባር በአፋር ክልል በማሸነፍ የክልሉን ስልጣን መልሶ በመያዙም እርሳቸው የክልሉ ፕሬዚደንት ሆነው መመረጣቸው ያስታወሱት ሃንፍሬ አሊምራህ፣ በ6 ወራት ውስጥ በማዕከላዊው መንግስት የተመራ ኩዴታ እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል። ከትግሉ ፍጻሜ በኋላ በአንድ አውሮፕላን አብረዋቸው አዲስ አበባ የተጓዙት የህወሃት መሪዎች አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ስዩም መስፍን የገቡትን ቃል ማፍረሳቸው ጠቅሰዋል።
በአፋር ተወላጆች ላይ ቀጥተኛና ጉልህ ተሳትፎ የአፍሪካ ኩዌት ይባል የነበረው የአፋር ክልል ዛሬ ያለው ኢንቨስትመንት ሙሉ በሙሉ በትግራይ ተወላጆች እጅ መውደቁን፣ የአፋር ተወላጁ ተመልካችና አገልጋይ ሆነው መቀመጣቸውን ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ ገልጸዋል።
የአፋር ህዝብ ከፍተኛ መከራ ወርዶበታል፣ ይህም መከራ በሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ላይም እየደረሰ ነው ያሉት ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ፣ ኦሮሞዎችንና አማሮችን እንዲሁም ሌሎች የጀመሩትን ትግል የአፋር ህዝብም የሚቀላቀሉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል በማለት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ በክልሉ እንደሚታይ ጠቁመዋል።
ዝርዝር ውስጥ በመግባት ለጠላት መረጃ አላቀብልም ያሉት ሱልጣን ሃንፍሬ አሊምራህ፣ የሚመጣውን እንደርስበታለን ሲሉ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አብራርተዋል። የአፋር ህዝብ ያለበት ስፍራ ስትራቴጂክ በመሆኑ ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ እንደሚኖርም አስታውቀዋል።
ሱልጣን ሃንፍሬ አሊምራህ በመጨምረሻ ባስተላለፉት መልዕክት ትግል የጀመሩት ኦሮሞዎችና አማሮች እንዲበረቱ፣ ሌሎችም አርዓያነቱን ይከተሉ ዘንድ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።