የአፋርና የሶማሌ ክልል በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ወደርሃብ ሊቀየር ይችላል ተባለ

ኢሳት (ጥር 2 ፥ 2008)

በደቡብ የአፋርና የሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን የሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ተከስቶ የሚገኘው የድርቅ አደጋ በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ወደርሃብ ሊቀየር እንደሚችል አንድ አለም አቀፍ ተቋም አሳሰበ።

በደረጃ ሶስት የድርቅ አደጋ ውስጥ ተፈርጀው የሚገኙት እነዚሁ አካባቢዎች አፋጣኝ እርዳታን ካላገኙ ወደ “ረሃብ” ደረጃ በሚመደበው ደረጃ አራት ሊሸጋገሩ ኣንደሚችሉ ድርጅቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለአስችኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎችን ቁጥር 10.2 ሚሊዮን እንደሆነ ቢግልፅም፣ ፋሚን ኧርሊ ዋርኒንግ ሲስተም የተሰኘው ተቋም የተረጂዎቹ ቁጥር ከህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ 15 ሚሊዮን መሆኑንም አመልክቷል።

በደቡብ የአፋርና የሶማሊ ሲቲ ዞን ውስጥ ከሚገኙት ቀበሌዎች በተጨማሪ በምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ ዞን የሚገኙ ቀበሌዎችም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸው እንደሚገኝ ተውቋል።

በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች በሚገኙ ከ180 በላይ ወረዳዎች ውስጥ ተከስቶ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ ወደከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ መምጣቱን በርካታ የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።

በአብዛኛው የትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ሶማሊያ ደቡብ ክልል የሚገኙ ዞኖች በደረጃ ሶስት የድርቅ አደጋ ውስጥ ተፈርጀው እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።

በቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ውስጥ ተረጂዎች ወቅታዊ የእርዳታ አቅርቦትን የማያገኙ ከሆነም ችግሩ አስከፊ ገጽታን ሊይዝ እንደሚችል የእርዳታ ድርጅቶች አሳስበዋል።

ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከተጋለጡት ኢትዮጵያዉያን መካከል ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑት ህጻናት ሲሆኑ፣ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡትም በአስከፊ ሁኔታ ውስት መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።

የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በአገሪቱ ለሶስት ወር የሚበቃ የእህል ክምችት አለ ሲሉ በቅርቡ መግለጻቸው የታወሳል።

ይሁንና፣ የተባበሩት መንግስትና የዕርዳታ ተቋማት ተረጅዎች ወቅታዊ እርዳታን እያገኙ እንዳልሆነ በመግለጽ የድርጅቱ አደጋ አስከፊ ይዘትን ኣየያዘ መምጣቱን አመልክተዋል።