ህዳር 14 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 26 ቀን በሞት በተለዩት አባታቸው በቢትወደድ ሱልጣን አሊሚራ ምትክ፤ ሰሞኑን እጅግ በደመቀ በዓል የሱልጣንነት ማዕረግ የተጎናፀፉት ሀንፍሬ አሊ ሚራ፤ በበዓለ-ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር በመንግስት ላይ ቅሬታ እንዳላቸው መንፀባረቁን ሪፖርተር ዘገበ።
“የአፋር ህዝብ ልብ፤ከመንግስት?ወይስ ከሱልጣን?” በሚል ርዕስ ጋዜጣው እንደዘገበው፤ የሀንፍሬ አሊሚራህን የሱልጣን ሲመት ለማክበር በኤርትራና በጅቡቲ የሚገኙትን ጨምሮ በአራቱም ማዕዘን የሚገኙ አፋሮች ወደ በ ዓሉ ስፍራ በመምጣት አይሳኢታ ከተማን አጨናንቀዋት መሰንበታቸውን አመልክቷል።
በጂቡቲ በጠቅላይ ሚኒስትር ዳላይታ አሕመድ ዶላይታ የተመራና በርካታ ሚኒስትሮችን የያዘ የመንግሥት ልኡካን ቡድንም በስፍራው ተገኝቷል። በዚሁ የሡልጣን ሐንፍሬ አሊምራሕ ሹመት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድርም የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮችን በመምራት በስፍራው ተገኝተዋል።
ከሦስት ወር በላይ ዝግጅት እንደተደረገበት የተነገረው ይኸው በዓል፣ በመቶ ሺዎች ብር ወጪ እንደተደረገበት ታውቋል። እንደ ሪፖርተር ዘገባ፤ደርግን በመቃወም የአፋር ነፃ አውጪ ግንባርን መሥርተው ሊቀመንበርነት የመሩት የያኔው ታጋይና የአሁኑ ሡልጣን ሐንፍሬ አሊምራሕ፣ በዚሁ ታላቅ በዓል ባደረጉት ታሪካዊ ንግግርም አፅንኦት ከሰጡዋቸው ጉዳዮች መካከል፣ አፋሮች የኢትዮጵያን ነፃነት በማስከበር በኩል ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ ሕዝቦች ቢሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት ‹‹በወባና በጉንፋን እያለቁ ያሉት ብቸኛ ሕዝቦች›› መሆናቸውን ነው፡፡
በጭብጨባና በአፋር ባህላዊ የደስታ መግለጫ ድምፅ በታጀበው በዚሁ ንግግራቸው ለአፋር ሕዝቦች፣ ለሦስቱም መንግሥታት ማለትም ለ ኢትዮጵያ፣ ለ ኤርትራና ለጅቡቲ ፤ ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ሐሳቦችን ማስተላለፋቸውም ተሰምቷል።
በተለይ፤ “የትም ይሁን የት አንድ አፋር ሲጨቆን ዝም ብዬ አላይም” ማለታቸው፤ የበዓሉን ዕድምተኞች ያስፈነደቀ ነበር ተብሏል። አባታቸውን አሊ ሚራህን የሚያወድሰውና-ልክ እንዳባታቸው ሁሉ ከእርሳቸውም ጋር ተባብሮ ለመስራት መንግስት ቃል እንደገባ የሚጠቅሰው የአቶ መለስ ንግግር በተወካያቸው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ በ አቶ አሚን አብድልቃድ አማካይነት ቀርቧል።
ለተገባው ቃልና ለቀረቡት ሙገሳዎች በበኩላቸው ምስጋና ያቀረቡት አዲሱ ሡልጣን ሐንፍሬ አሊምራሕ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጅታቸውን ያረጋገጡ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቅሬታ ቢጢ እንደተሰማቸው ጠቆም ሳያደርጉ አላለፉም-“የኢትዮጵያ መንግስት በልጃችንም በኩል ቢሆን ለላከልን መልዕክት እናመሰግናለን” በማለት።
ጋዜጣው ዘገባውን ሲቋጭም፦” በዚህ ንግግራቸው ለአፋር ሕዝብ ያላቸውን ወገንተኝነት በስፋት ያንጸባረቁት ሡልጣን ሐንፍሬ አሊምራሕ፣ በቀጣይነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለሚኖራቸው ግንኙነትና ትብብር አቅጣጫ የጠቆሙ ቢሆንም፣ ከምንም ዓይነት የፍትሕ መጓደልና ከኋላቀር አስተዳደር ጋር የሚደራደሩ አይመስሉም፡፡ የአሳኢታንና የመላው አፋርን ስሜት የነካውም ይሄ ሳይሆን አይቀርም”ብሏል።
የኢትዮጵያ፣ የ ኤርትራና የጂቡቲ አፋሮች በአንድ የተሰባሰቡበት ይህ የሱልጣን ርክክብ ሹመት በትንሹ በ60 ዓመት አንድ ጊዜ የሚታይ ትዕይንት መሆኑን የበዓሉ ዕድምተኞች ተናግረዋል።
“ሱልጣን አሊ ሚራህ፦”እንኳን እኛና ግመሎቻችንም የ ኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቋታል” በሚለው ታሪካዊ ንግግራቸው ሲታወሱ ይኖራሉ።