(ኢሳት ዲሲ–ጥር 29/2010)
የአጼ ቴድሮስ ሐውልት በደብረታቦር ከተማ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት ተመረቀ።
በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ በ2 ሚሊየን ብር ወጪ የተሰራው የአጼ ቴድሮስ ሃውልት 7 ነጥብ 5 ሜትር ርዝመት ያለው ነው።
በኢትዮጵያ የንግስና ታሪክ ከ1847 እስከ 1860 ኢትዮጵያን የመሩት አጼ ቴድሮስ የሀገር አንድነት ተምሳሌት ናቸው።
በከፋፍለህ ግዛው ስልት በተነጣጠለ ሁኔታ በኢትዮጵያ የነበረውን የዘመነ መሳፍንት አገዛዝ ለማስወገድ ደፋ ቀና ያሉት አጼ ቴድሮስ በእንግሊዞች አልማረክም ብለው ራሳቸውን በገዛ እጃቸው ያጠፉ መሪም ናቸው።
እጅ መስጠት የሀገርን ክብር ማዋረድ ነው ብለው ራሳቸውን የሰውትን አጼ ቴድሮስን የሚያስታውስ ሀውልት በደብረታቦር አደባባይ ቆሞላቸዋል።
ሀውልቱ የተሰራው በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ በተመደበ በጀት መሆኑ ነው የተገለጸው።
ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገበትና በደብረታቦር ከተማ የተገነባው የአጼ ቴድሮስ ሃውልት የሴቫስቶፎል መድፍ ያለበትና ጦር ይዘው በቁማቸው የሚታዩበት ነው።
ሀውልቱ ሲመረቅ በርካታ የደብረታቦር ህዝብ በአደባባዩ ዙሪያ ታድሞ አጼ ቴድሮስን ሲያስታውስና ሲያከብር ውሏል።
የአጼ ቴድሮስ ሃውልት በደብረታቦር መመረቅ ትውልዱ ለአንድነቱ ያለውን ጽናት አሁንም እያሳየ መሆኑን እንደሚያመላክት ታዛቢዎች ይናገራሉ።