የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ እየተባባሰ ነው ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 16 ፥ 2008)

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የተቀሰቀሰውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ መባባስን ተከትሎ ለጊዜያዊ የህክምና መስጫ የተቋቋሙ ጣቢያዎች ወደ 24 ከፍ እንዲሉ መደረጉን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ሲባል የከተማዋ ነዋሪዎች ለማንኛውም አገልግሎት የሚጠቀሙትን ውሃ አፍልተው እንዲጠቀሙ ሚኒስቴሩ ጥሪውን አቅርቧል።

በመዲናይቱ አዲስ አበባ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታን ለማከም የህክምና ሰርቲፊኬት በሌላቸው የህክምና ተቋማት በበሽታው የተያዙ ሰዎችን እንዳይታከሙ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አሳስቧል።

በበሽታው የተጠረጠሩ በርካታ ነዋሪዎች ወደ ግል ተቋማት ለህክምና በመሄድ ላይ ቢሆኑም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ታካሚዎች ከበሽታው መፈወሳቸው ሳይረጋገጥ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው ሲሉ ቅሬታን አቅርቧል።

ታማሚዎች በግል የህክምና መስጫ ተቋማት የሚያደርጉት ህክምና በሽታውን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሚገኝ በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ አህመድ ኢማኖ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በመሰራጨት ላይ ያለው ይኸው በሽታ በወረርሽኝ መልክ ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን የህክምና ባለሙያዎች በድጋሚ አስታውቀዋል።

ወደግል የህክምና መስጫ ተቋማት በመሄድ ላይ ያሉ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው የበሽታው ስርጭት ስጋት ስለሆነባቸው ህዝብ በብዛት ወዳሉባቸው ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ተቋማት ከመሄድ መቆጠባቸውን በመግለጽ ላይ እንደሆኑ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ ጥሪው ከተላለፈ በኋላ የህክምና መስጫ ተቋማቱ ታማሚዎችን ወደ ጊዜያዊ ጣቢያዎች ብቻ እንዲልኩ አሳስቧል።

በከተማዋ ያለው የውሃ እጥረት የበሽታው ስርጭት እንዲዛመት አስተዋፅዖ ያደረገ ሲሆን፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የከተማዋ ነዋሪዎች ለማኝናውም አገልግሎት የሚጠቀሙትን ውሃ አፍልተው ብቻ እንዲጠቀሙ አሳስቧል።

ለመዲናይቱ በተጨማሪ በስድስት የኦሮሚያ ክልል ዞኖችና በሶማሊ ክልል በመሰራጨት ላይ ባለው በዚሁ በሽታ 19 ሰዎች ሞተው ከ2ሺ የሚበልጡ ደግሞ በህክህምና ላይ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።