ኢሳት (ሚያዚያ 12 ፥ 2008)
በድርቅ በተጎዱ ሶስት ክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ በተቀሰቀሰ የአጣዳፊ ተቅማጥ ወረርሽን በትንሹ 14 ሰዎች ሞተው ከ1ሺ የሚበልጡ ደግሞ በበሽታው መያዛቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
ይኸው በኦሮሚያ፣ የደቡብ እንዲሁም የሶማሊ ክልሎች የተቀሰቀሰው ወረርሽኝ በ15 ወረዳዎች ውስጥ ተዛምቶ የሚገኝ ሲሆን በሽታው ወደ አጎራባች ክልሎች ይዛመታል ተብሎም ተሰግቷል።
እስከሳምንቱ መገባደጃ በደረሰው የበሽታው ወረርሽኝ በትንሹ 14 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉንና 1ሺ 344 ነዋሪዎችም በበሽታው መያዛቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድርቁ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
የአጣዳፊ ተቅማት በበሽታው በኦሮሚያ ጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ በሊበን ወረዳም ተመሳሳይ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያለው የውሃ እጥረትና በቅርቡ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ለወረርሽኙ መከሰትም ምክንያት መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።
የአለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ በሽታው ወደሌሎች አጎራባች ወረዳዎችና ክልሎች ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋትም እንዳሳደረ ድርጅቱ በሪፖርቱ አስፍሯል።
የአጣዳፊ ተቅማት በበሽታው በቅርቡ በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያዋ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች ተከስቶ ከ40 የሚበልጡ ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸው ይታወሳል።
በሶስቱ ክልሎች በበሽታው የተያዙት 1 ሺህ 344 ሰዎች በአሁኑ ሰዓት አስቸኳይ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፣ ወረርሽኙ አስቸኳይ ቁጥጥር ካልተደረገበት በቶሎ ተዛማች መሆኑም የጤና ባለሙያዎች ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ተመሳሳይ በሽታዎች በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
የበሽታው ወረርሽኝ እንዳይከሰት ለማድረግም የጤና ተቋማት ቅድመ ዝግጅት እያከናወኑ እንደሆነ አስተዳደሩ አስታውቋል።