(ኢሳት ዲሲ–ጥር 9/2011)የአድዋን ድል ኢትዮጵያውያን በየተሰማሩበት መስክ መድገም እንዳለባቸው አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ ገለጸች።
አትሌት ደራርቱ የአድዋን ድል ለመዘከር በተዘጋጀው የሩጫ ውድድር ላይ በባዶ እግሯ 500 ሜትር ልትሮጥ መዘጋጀቷንም አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ከአድዋ ድል መታሰቢያ አንድ ቀን በኋላ በአዲስ አበባ በተዘጋጀው የ10 ኪሎሜትር ሩጫ ላይ አትሌት ደራርቱ የምትሳተፍ ሲሆን 500 ሜትሩን ያለጫማ ለመሮጥ ወስናለች።
የዚሁ ውድድር አምባሳደር ተደርጋ የተሰየመችው አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለአድዋው ሩጫ ልምምድ ሰርቼ 9 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩን በጫማ የተቀረውን 500 ሜትር በባዶ እግሬ ለመሮጥ ቃል እገባለሁ ማለቷ ተገልጿል።
በአድዋ ድል እናቶችና አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው ያቆዩትን ታሪክና ጀግንነት ሁሉም በተሰማራበት መስክ ውጤታማ በመሆን በስራው ጀግና መሆን አለበት ስትል አትሌት ደራርቱ መልዕክት አስተላልፋለች።
የባርሴሎና ኦሎምፒክ ጀግና ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ስትሆን በቅርቡም የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጧም የሚታወስ ነው።