ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2008)
በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለውን የመሬት ዘረፋና የጅምላ ጭፍጨፋን በመቃወም ላይ በነበሩ በአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ተቃውሞውን ለማስቆም በተሰማሩ የጸጥታ ሃይላት መካከል ግጭት እንደተፈጠረ የአይን እማኞች ከስፍራው አስታወቁ።
ሰኞ ጠዋት የተጀመረው ይህ ተቃውሞ፣ ተማሪዎቹ በአዳማ ዩንቨርስቲ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ በኦሮሚያ ክልልና በሌላው የኢትዮጵያ ክልሎች ላይ እየደረሰ ያለው ጭፍጨፋና፣ ወከባና፣ እንግልትን እንዲቆም ሲጠይቁ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
አመጹን ለማስቆም ቀደም ብሎ በአካባቢው የሰፈረው ብዛት ያለው የአጋዚ ክፍለጦር እንደተሰማራ የተገለጸ ሲሆን፣ ተማሪዎችም ከመሬት ወረራና ከሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጨማሪ የአጋዚን በትምህርት ማዕከል መስፈር በጽኑ ተቃውመዋል።
ተቃውሞ እየተደረገ በነበረበት ወቅት የአጋዚ ክፍለጦር አባላት ተማሪዎች ላይ ጥይት እንደተኮሱና፣ ተማሪዎች ደግሞ ራሳቸውን ለመከላከል ይሯሯጡ እንደነበር የአይን እማኞች ገልጸዋል። የአጋዚ ወታደሮች አስለቃሽ ጋዝ በዩንቨርስቲ ግቢ እንደተጠቀሙ እነዚሁ የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
በግጭቱም ወቅት አንድ ተማሪ እንደተገደለ ሲታወቅ፣ በጥይት የቆሰሉ ተማሪዎች ደግሞ በአምቡላን ወደሆስፒታል ተወስደዋል። የአጋዚ ወታደሮች ብዛት ያላቸው ተማሪዎችን እየደበደቡ ጉድጓድ ውስጥ እንደወረወሯቸው የአይን እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።
የፖሊስን ጥይት፣ አስለቃሽ ጋዝና፣ ዱላ ለማምለጥ ብዛት ያላቸው ተማሪዎች ከአዳማ ዩንቨርስቲ ጀርባ በሚገኘው ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ተጠልለው የነበረ ቢሆንም፣ የአጋዚ ሃይሎች ወደዚያ በመሄድ ተማሪዎችን እየደበደቡ እንዳስወጧቸው ታውቋል። በኋላም አብዛኞቹን ተማሪዎች ከቤተክርስቲያን አስወጥቶ በማሰለፍ ወደ ግቢ ይዘዋቸው ሄደዋል ተብሏል። የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎችም የፖሊስን ድርጊት ዝም ብሎ ከማየት ውጭ ምንም ነገር ማድረግ አለመቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ የአጋዚ ክፍለጦር ወታደሮች የአውቶቡስ መነሐርያን በመዝጋት ተማሪዎች ወደቤተሰቦቻቸው እንዳይሄዱ እንዳደረጉ ታውቋል። አውቶቡስ ተራ የሚገባ ሰው መታወቂያ እያሳየ እንደነበርና፣ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ግን ወደግቢው እንዳይገቡ እንዳልተፈቀዳላቸው የአይን እማኞች ለኢሳት ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ የገለጹ ቢሆንም፣ የአጋዚ ወታደሮች ግን ያለርህራሄ ተማሪዎች እየደበደቡ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
የኦሮሚያ ፖሊስ በአካባቢው ቢኖርም፣ ተማሪዎችን ይደበድቡና ያዋክቡ የነበሩት ግን የታጠቁ እና ለውጊያ ዝግጁ የሆኑ የመደበኛ ሰራዊት አባላት እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
የማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ግጭት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የዩንቨርስቲ ግቢ በከባድ መሳሪያ ጭምር እየተጠበቀ እንደሆነ የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በሃረማያ፣ አምቦ፣ ዲላ፣ እና በሁሉም በአገሪቱ ባሉት ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሁለት ወራት በተካሄደ ተቃውሞ፣ ከ125 በላይ የሚሆን የሰው የህይወትና ከፍተኛ ንብረት መውደሙ ይታወቃል። አሁንም በአብዛኛው የኦሮሚያ ክፍሎች ከፍተኛ ግጭቶት እየተከሰቱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።