የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው

ሚያዚያ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሰራተኞች ለኢሳት እንደተናገሩት የዩኒቨርስቲው ሀላፊዎች ከዚህ በፊት ተሞክሮ  ውጤት ያላስገኘውን ቢፒአር በድጋሚ እንዲጀመር በማድረጋቸው ሰራተኛውን እያሰቃዩት ነው በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ሰራተኞች የትምህርት ደረጃቸውንና የሚፈልጉትን የስራ መስክ  እንዲገልጹ ቢደረግም፣ በመጨረሻ ላይ ግን አብዛኞቹ ሰራተኞች ለቦታው አትመጥኑም ተብሎ ተነግሯቸዋል። እንደ ምንጮች ከሆነ  ከ20 አመት ላናነሰ ጊዜ ያገለገሉ ሰራተኞች የትምህርት ደረጃቸውን በማሻሻል ለተመደቡበት ቦታ ተገቢውን የትምህርት ማስረጃ ቢያቀርቡም ሀላፊዎቹ ግን ያገልግሎት ዘመናቸውን ውድቅ በማድረግ፣ ከዜሮ እንዲጀምሩ እያደረጉዋቸው ነው። ሀላፊዎቹ የወሰዱት እርምጃ ነባር ሰራተኞችን አበሳጭቷል። አንዳንድ ሰራተኞች  እርምጃው መንግስት ነባር ሰራተኞችን በማባረር አዳዲስ የኢህአዴግ አባላትን በቦታቸው ለመተካት በማሰቡ የተወሰደ እርምጃ ነው።

መንግስት ቢፒአር የተባለው አሰራር ውጤት ሊያመጣ እንዳልቻለ በተደጋጋሚ ከገለጸ በሁዋላ፣ ተመልሶ ይህንን አሰራር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከሩ አነጋጋሪ ሆኗል።