የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ህገመንግስቱን ጨምሮ የፖለቲካ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ አቀረቡ

ኢሳት ( መስከረም 13 ፥ 2009)

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ህገመንግስቱን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ የፖለቲካ ስርዓቶች ማሻሻያ እንዲደረግ ለመንግስት ጥያቄያቸውን አቀረቡ። ላለፉት 5 ቀናቶች ሲካሄድ በቆየው አገር አቀፍ የመምህራን መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የዩኒቨርስቲው መምህራን የጋራ አቋም በመያዝ አበይት የተባሉ ጥያቄዎች ለመንግስት እንዲቀርብላቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ከዜና ክፍላችን ጋር ቃለምልልስ ያደረጉ መምህራን አስረድተዋል።

የመንግስት ተወካዮች ለመወያያ ያሏቸውን ነጥቦች ለመምህራኑ ቢያቀርቡም ተሳታፊ የነበሩ መምህራን ወቅታዊ የሃገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች አጀንዳ ሆነው እንዲቀርቡ ተደጋጋሚ ጥያቄን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ይኸው የምክክር መድረክ አርብ በተጠናቀቀ ጊዜ ተሳታፊ የነበሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን አምስት አበይት ነጥቦች በማንሳት በማጠቃለያ ሃሳቡ ላይ እንዲካተትላቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል።

ህገመንስቱን ጨምሮ ወቅታዊ በሆኑ የሃገሪቱ የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ የጠየቁት መምህራኑ በኢትዮጵያ በአብዛኛው እየተከሰተ ያለው ችግር ገዢው መንግስት የፈጠረው እንዲሆነ መግለጻቸውን ከኢሳት ጋር ቃለምልልስ ያደረጉ መምህራን አስረድተዋል።

የብሄር ፖለቲካ ወቅታዊ የሃገሪቱ የፖለቲካ ጉዳይ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ሌሎች አበይት ጉዳዮች በመንግስት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው መምህራን ካቀረባቸው ነጥቦች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ከመምህራን የቀረቡ ጥያቄዎችን አብዛኞቹ ጥናትን የሚፈልጉ ናቸው በማለት ለመምህራኑ ምላሽን ቢሰጡም መምህራኑ አብዛኞቹ ነጥቦች በገሃድ የሚታዩ ችግሮች ናቸው በማለት ምላሽን እንዲሰጡ መምህራኑ ገልጸዋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተጨማሪ ባህር ዳር ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ሲካሄዱ የነበሩ የውይይት መድረኮች ተመሳሳይ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

በሃገር አቀፍ የውይይት መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩ መምህራን መንግስት ካቀረበው አጀንዳ በተጨማሪ ወቅታዊ የሃገሪቱ የፖለቲካና ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አጀንዳ ሆነው እንዲቀርቡ ጥያቄን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

በተለያዩ የውይይት መድረኮች መምህራን ያነሱት ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ ባለማግኘቱ ምክንያት በውይይቱ ምንም አይነት አስተየየት ባለመስጠት ተቃውሞን ሲያሳዩ እንደነበር ከኢሳት ጋር ቃለ-ምልልስን ያደረጉና ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ መምህራን አስረድተዋል።

ከመምህራን ጋር ለአንድ ሳምንት ያህል ጊዜ ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ አርብ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ቀጣይ ውይይቶች ከወላጆች ጋር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ከመምህራንና ወላጆች ጋር ሊካሄድ የታቀደውን የውይይት መድረክ ተከትሎ መስከረም 3 ፥ 2009 ዓም ይጀምራል ተብሎ የነበረው የዘንድሮ የትምህርት ዘመን ለመስከረም 18 እንዲዛወር መደረጉ ይታወሳል።