የአዲስ አበባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ተባብሷል

ኀዳር (ሦስት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :- በአዲስአበባ ከተማ በርካታ አካባቢዎች የ24 ሰዓታት የውሃ አቅርቦት ማግኘት ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ

ነዋሪዎች ሥራቸውን በመተው ውሃ ለማግኘት ከሰፈር ሰፈር እንዲንከራተቱና ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን ዘጋቢያችን ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስአበባ በየትኛውም አካባቢ የመጠጥ ውሃ ችግር ተባብሶ መቀጠሉን የጠቆሙት  ነዋሪዎች አስተዳደሩ በየጊዜው ተስፋ ከመስጠት ባለፈ በተጨባች ችግሮቹን መፍታት አልቻለም ብለዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በየቤታቸው

በርሜሎችን በማዘጋጀት ውሃ ሊጠፋ ይችላል በሚል ሃሳብ አንዳንዴ ሌሊቱን ሙሉ ውሃ ሲሞሉ የሚያነጉበት ሁኔታ የኑሮአቸው አንድ አካል መሆኑ እንደሚሳዝናቸው ተናግረዋል፡፡

የሚጠጠት ውሃ በቋሚነት ከመጥፋት ጋር ተያይዞ የአንድ ሊትር የታሸገ የፋብሪካ ውሃ በአዲስአበባ በአማካይ እስከ10 ብር እየተሸጠ መሆኑ ለማረጋገጥ ተችሎአል፡፡

የአዲስአበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ባካሄደው ጥናት ለከተማዋ ነዋሪ በቀን የሚያስፈልገው ውሃ መጠን 600 ሺ ሜትር ኪዩብ ሲሆን በትክክል እየቀረበ ያለው ግን ግማሽ ያህሉ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ 260ሺ ሜትር

ኪዩብ ውሃ ለማቅረብ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ነው ቢባልም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከሚመጣው ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር ችግሩ በአጭር ጊዜ የመቀረፉ ጉዳይ አጠራጣሪ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በተለይ በአዳዲስ የማስፋፊያ አካባቢዎች ውሃ አልባ በመሆናቸው ነዋሪዎች የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት ጨርሶ እንዳልቻሉ፣ ብዙዎችም አዲስ ወደሰሩት ቤት እንዳገቡ ውሃ ትልቅ ምክንያት በመሆኑ ለቤታቸው ጥበቃ ከመቅጠር ጀምሮ

ለሚኖሩበት የቤት ኪራይና የትራንስፖርት ክፍያ አላስፈላጊ ወጪዎች እየተዳረጉና ኑሮአቸው እየተቃወሰ መሆኑን ሮሮአቸውን በማሰማት ላይ ናቸው፡፡

አስተዳደሩ በ2007 በጀት ዓመት ዕቅዱ ከውሃ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ሕዝቡ በየጊዜው የሚነሳቸውን ችግሮች በአግባቡና በወቅቱ ለመፍታት እንደሚሰራ ቢያመለክትም እንዴትና በምን መልክ ችግሩን በአጭር ጊዜ ሊፈታ እንደሚችል ያስቀመጠው ግልጽ አቋም የለም፡፡ አስተዳደሩ በዚህ ዕቅዱ የውሃ ስርጭቱን

ፍትሀዊነት ለማረጋገጥ 80 በመቶ የሚሆነውን የከተማ አካባቢ የ24 ሰዓታት ያልተቋረጠ የውሃ ስርጭት እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሚሰራ በዕቅዱ ላይ ያስቀመጠ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ምን ያህል አካባቢዎች የ24 ሰኣታት ውሃ እንደሚያገኙ ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡በአዲስአበባ ከተማ በተመሳሳይ መልኩ የኤሌክትሪክ ኃይል ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ መቆራረጡ ተባብሶ መቀጠሉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በሌላ ዜና ደግሞ መንግስት ስኳር አስገብቶ ማከፋፈል መጀመሩንም ቢያስታውቅም ችግሩ አሁንም አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሎአል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደገለጹት እስካሁን ስኳር በውድ ዋጋ ሲገዙ ቢቆዩም ያለፉትን ሳምንታት በየትኛውም ዋጋ ለማግኘት አልቻሉም።

መንግስት ችግሩ ሁሉም የስኳር ፋብሪካዎች ስራ ሲጀምሩ ይቀረፋል ቢልም የጊዜ ገድብ ግን አላስቀመጠመም።