ታህሳስ ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በመጪው እሁድ ታህሳስ 7፣ 2005 ዓም አለአግባብ የታሰሩ የሙስሊም ማህበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን፣ ጋዜጠኞችንና የተቃዋሚ መሪዎችን በቃሊቲ ተገኝተው ለመጠየቅ የወጠኑት እቅድ ጥሩ ምላሽ እያገኘ መምጣቱን አዘጋጆች ገልጸዋል።
ማንኛውም የህገመንግስቱን የእምነት እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መከበር እንዳለበት የሚደግፍ ኢትዮጵያዊ በሙሉ ወደ ቃሊቲ በመሄድ ድጋፉን እንዲያደርግ እንጠይቃለን የሚል መግለጫ ካወጡ በሁዋላ ጥሪው በማህበራዊ ድረገጾች ከመሰራጨት አልፎ በአዲስ አበባም ህዝቡ እየተነጋገረበትነው ብለዋል።
ህገመንግስቱ የሰጣቸውን መብት በመጠቀም መላው ህዝባቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ የሰላም እና የነጻነት ታጋዮች በእስር ቤት እየማቀቁ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዝም ብሎ የሚመለከት ከሆነ የታሪክ እና የትውልድ ተጠያቂነት ይኖርበታል በማለት አዘጋጆች ገልጸዋል።
ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ በርካታ ኢትዮጵያውያን በግፍ እስር ላይ እንደሚገኙ የገለጡት አዘጋጆች፣ የሙስሊም መሪዎችን ጨምሮ ፖለቲከኞችን አቶ አንዱለአም አራጌን፣ ክንፈሚካኤል ደበበ ( አበበ ቀስቶ)፣ ምትኩ ዳምጤ፣ ናትናኤል አለሙ፣ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ሊሌሳ፣ ጋዜጠኞችን እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙ፣ ውብሸት ታየና ሌሎችንም የህሊና እስረኞች የመጠየቅ ፍላጎቱ አላቸው።
አልጀዚራ ባለፈው ሳምንት ለጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለታሰሩት የህሊና እስረኞች ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በእስር ላይ የሚገኙት አሸባሪዎችና ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው እንጅ የህሊና እስረኞች አይደሉም በማለት መልሰዋል።