ጥር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የከንቲባ ጽ/ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት አቶ አሰግድ ጌታቸው ይመኑ ጥር 29 ቀን 2006 ዓም ለሁሉም የመስተዳድሩ ቢሮችና ለክፍለከተሞች በጻፉት ደብዳቤ ፣ ማንኛውም በግቢው ውስጥ የሚያድር መኪና የማን እንደሆነ ለማወቅ ይቻል ዘንድ ታርጋቸው ተገልጾ ይቅረብልን ብለዋል። ደብዳቤው በግልባጭ ለግቢው ጸጥታ ዴስክ ተመርቷል።
መስተዳድሩ ይህን ደብዳቤ የጻፈው ኢሳት በቅርቡ በመስተዳድሩ ግቢ ውስጥ ከ280 በላይ አዳዲስ ዘመናዊ አውቶሞቢሎች በውድ ዋጋ ተገዝተው መቆማቸውን ከዘገበ በሁዋላ ነው። መስተዳድሩ ይህን ደብዳቤ ሲጽፍ በግቢው ውስጥ የሚቆሙ መኪኖችን አይነትና ብዛት እንደማያውቅ እንዲሁም ንብረቱንም ለይቶ እንደማያውቅ ያሳያል በማለት ሰራተኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ የመንግስት ባለስልጣናት የ7 ሚሊዮን ብር ኮብራዎችን መግዛት እንዲያቆሙ መጠየቃቸው ይታወሳል።