የአዲስ አበባ አስተዳደር በከፍተኛ የበጀት እጥረት ውስጥ መግባቱ ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 16/2010)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከፍተኛ የበጀት እጥረት ውስጥ መግባቱ ተገለጸ።

ከፍተኛ ገቢ የሚጠበቅበት የመሬት ሊዝ ጨረታ ላለፉት 8 ወራት አልተካሄደም።

መስተዳድሩ በግማሽ አመቱ እሰበሰባለሁ ብሎ ካቀደው ማግኘት የቻለው ከግማሽ በታች ነው።እንደ ሪፖርተር ዘገባ ከሆነ የተሰበሰበው ገቢ የአስተዳደሩን የመደበኛ ወጪ ከመሸፈን የሚያልፍ አይደለም።በአመቱ ይሰራሉ ተብለው በእቅድ የተያዙ ካፒታል ፕሮጀክቶች ከእቅድ እንደማይዘሉ ጨምረው ገልጸዋል።

በሃገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ፣የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣የንግድና አገልግሎት ተቋማት መዳከም፣ነጋዴውና የከተማው ነዋሪ ለመስተዳድሩ ግብር ለመክፈል ፍላጎት ማጣትና የአስተዳደሩ ሰራተኞች በፍላጎት ለመስራት ዝግጁነት ማጣት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች እንደሆኑ ተመልክቷል።

በሀገሪቱ ተፈጠረው የጸጥታ ችግርና የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የውጭ ኢንቨስተሮች ተሳትፎም እንደቀነሰ ማወቅ ተችሏል።

በ2009 በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በተሰናዳው የአለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ከ20 ሀገሮች በላይ የሚገኙ 160 በላይ የውጭ ኩባንያዎች የተሳተፉ ቢሆንም ፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው አውደ ርዕይ የተሳታፊዎች ቁጥር እንደሚቀንስ ታውቋል ።

ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳዩት 11 ሃገራት ብቻ እንደሆኑም መረዳት ተችሏል።በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከፍተኛ ገቢ የሚሰበስብበት የመሬት ሊዝ ጨረታ ላለፉት 8 ወራት ማካሄድ እዳልቻለ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።