የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በኢህአዴግ አመራር ተስፋ መቁረጣቸውን ተናገሩ

የካቲት ፩፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሚያዝያ ወር 2005 የሚካሄደውን የአዲስአበባ እና የአካባቢ ምርጫ ተከትሎ የኢህአዴግ ከፍተኛ ሹማምንት በዘመቻ ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር በየክፍለ ከተማው በጀመሩት ውይይት ከፍተኛ ትችት እያስተናገዱ መሆኑን በስብሰባዎቹ ላይ የተገኙ ምንጮቻችን ጠቆሙ፡፡

የወደፊቱ የከተማዋ ከንቲባ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁትን አቶ ድሪባ ኩማን ጨምሮ የአሁኑ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው፣የመንግስት ተጠሪ ሚ/ር ወ/ሮ አስቴር ማሞና ሌሎችም ሚኒስትሮች በተገኙባቸውና ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እየተካሄዱ ባሉ መድረኮች ሕዝቡ በኢህአዴግ አመራሮች ድክመት፣ ሙስናና ብልሹ
አሰራር ተስፋ መቁረጡን በድፍረት አስታውቋል፡፡

በስብሰባዎቹ ላይ ኢህአዴግ ይደግፉኛል ያላቸው ነዋሪዎች በጥንቃቄ ከየቀበሌው ተመርጠው እንዲገኙ የተደረገ ሲሆን፣  ብዛት ያላቸው እናቶችና ሽማግሌዎች እንዲሁም ጥቂት ወጣቶች ተገኝተዋል፡፡

በስብሰባዎቹ ላይ በርካታ ወጣቶች አለመገኘታቸውና የተገኙትም መረር ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቃቸው ኢህአዴግ ደጋፊና አባል በሚላቸው የራሱ ሰዎች ዘንድ ሳይቀር ከፍተኛ ትችት እየደረሰበት ነው።

ህዝብን ወደ ታች ወርዶ ለማነጋገር ድፍረት አጥተው የነበሩ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ይህን የምርጫ ወቅት አስታከው ሕዝቡን  “የኪራይሰብሳቢነት ችግሮች አሉብን፣የአመለካከት ችግሮች አሉብን፣የአፈጻጸም ችግሮች አሉብን” በሚል የተለመደ ፕሮፖጋንዳ በመደለል ችግሮቹን በቀጣይ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ ለማግባባት ቢሞክሩም አብዛኛው ሕዝብ በዚህ ሁኔታ የምትቀጥሉት እስከመቼ ነው በማለት እንዳፋጠጣቸው ታውቋል፡፡

በሁሉም መድረኮች በዋንኛነት የኑሮ ውድነት፣የስራአጥነት፣ከላይ እስከታች ያሉ ሹሞች የሚፈጽሙት ስርቆት በዋናነኝነት የተነሱ ሲሆን በኢህአዴግ ሰዎች በኩል ችግሮቹ መኖራቸውን በማመን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ ቢናገሩም ህዝቡ ግን በመልሶቹ እንዳልረካ በስፍራው የተገኙ ምንጮች ገልጸዋል።

በስብሰባዎቹ ላይ ሌብነትንና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አርአያ ሊሆኑ እንዳልቻሉ፣ እንዲያውም በሌብነት የሚጠረጠሩ አመራሮች መኖራቸው ሙስናን ለመታገል እንቅፋት እንደሆነባቸው አንዳንድ አባላት ተናግረዋል፡፡

በዝቅተኛ እና በከፍተኛ አመራሩ መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መናናቅ መፈጠሩ ወደሲቪል ሰርቪሱ ተሸጋግሮ ከላይ ወደታች የሚወርዱ መንግስታዊ ስራዎችን ጭምር በሕግና በስርዓት ለማስፈጸም እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን የተናገሩ አባላትም ነበሩ፡፡

“አንዱ የኢህአዴግ አመራር ሌላውን እየናቀ፣ ትእዛዝ ለማስተላለፍም ሆነ ትእዛዝ ተቀብሎ ለመፈጸም አስቸጋሪ ሆኗል በማለት የተናገሩት የኢህአዴግ አባላት፣ በተለያዩ አካባቢዎች  የሚታየው የስራ መጓተት የዚህ የመናናቅ ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል።

በየቦታው ለልማት እየተባለ ሕዝብን አለአግባብ የማፈናቀል ስራም ግንባሩን ከሕዝብ ጋር እያቆራረጠው መሆኑን አንዳንድ አባላት ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ አዜብን ጨምሮ የኢህአዴግ ዋና ዋና ሹሞች በአዲስ አበባ ያለ ተቃዋሚ ፓርቲ ብቻቸውን ይወዳደራሉ።

በአዲስ አበባ ኢህአዴግ በምርጫ 97 ሙሉ በሙሉ መሸነፉ ይታወሳል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነዋሪው ለምርጫ ያለው ፍላጎት መሟጠጡን ታዛቢዎች ይናገራሉ።