ሚያዚያ ፲፬(አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአዲስ አበባ ታክሲ እና የረጅም ርቀት ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች ከመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ የታሪፍ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው ለአዲስ አበባ እና ለፌደራል የትራንስፖርት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ያቀረቡት አቤቱታ ተግባራዊ ምላሽ ባለማግኘቱ ስራ ለማቆም እንደሚገደዱ አስታወቁ።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሁለት የአዲስአበባ ታክሲዎች ማህበራት አመራሮች ለአዲስ አበባው ዘጋቢያችን እንደተናገሩት፣ ባለፉት አምስት አመታት ብቻ ከ200 ፐርሰንት በላይ የመኪና መለዋወጫ እቃዎች ዋጋ ጭማሪ መታየቱን፣ የአንዳንዶቹም ዋጋ እስከ 500 ፐርሰንት የናረ መሆኑን በመግለጽ አሁን ባለው ታሪፍ ስራው አዋጪ ሊሆንላቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል።
ችግሩን ማህበራት በራሳቸው ወጪ አስጠንተው የታሪፍ ማሻሻያ እንዲደረግ ቢያቀርቡም ባለስልጣኑ ተስፋ ከመስጠት ውጪ በተግባር መፍትሄ ሊሰጠን አልቻለም ብለዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ የሀገር አቋራጭ አውቶቡሶችም ተመሳሳይ ጥያቄ ምላሽ መነፈጉ በዘርፉ የተሰማሩ ወገኖችን ቅሬታ አስከትሎአል።
በተለይ ታክሲዎች ከመለዋወጫ መወደድ ጋር ተያይዞ በየጊዜው እየቆሙ ከገበያ በመውጣት ላይ ናቸው ያሉት የማህበራቱ አመራሮች ሌሎቻችንም ለመለዋወጫ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣን መቀጠል ስለማንችል ስራችንን ለማቆም እንገደዳለን ብለዋል።