ኢሳት (ጥር 5 ፥ 2008)
የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተጠራቀሙ የጭቆናና አፈና ችግሮች እንዲፈነዱ ያደረገ ክስተት ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዙሪያ የመሬት መፈናቀል ጥናትና ምርምር እያደረጉ ያሉት አቶ ብርሃኑ ሌንጂሶ ለኢሳት ገለጹ።
መሬት ለመንግስት የስልጣን ምንጭ፣ ለገበሬው የህልውና መሰረት ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ መንግስት የህልውና መሰረት የሆነውን የገበሬውን መሬት በመንጠቅ እንደማስፈራሪያ እየተጠቀመበት እንደሆነ ለኢሳት ገልጸዋል።
የመሬት ቅርምት ማለት ያልተተገበረ ልማታዊ ዕቅድ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ የአሁኑ የአዲስ አበባ የመሬት ፕላን ተቃውሞ የብዙ አመት የተጠራቀመ ብሶትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ማስተንፈሻ ሆኖ ያገለገለ ክስተት እንጂ ራሱን ችሎ አመጽ ያስነሳ ችግር እንዳልሆነ ለኢሳት ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አስከፊ የጭቆናና የድህነት ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት ብርሃኑ፣ ባለስልጣናቱና ቤተሰቦቻቸው ግን በመሬት ቅርምት በልጽገው ይገኛሉ ብለዋል። የተቀናጀ ማስተር ፕላን የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄ አለመሆኑን ለማስረዳት በአዲስ አበባ ከተማዋ ዙሪያ ያሉ መሬቶችን ባለስልጣናት በራሳቸውና በዘመዶችቻቸው ስም ተከፋፍለው እንደጨረሱት አስረድተዋል።
ኦህዴድ ማስተር ፕላኑን አስቁሜያለሁ ያለው እውነትነትን በተመለከተ የተጠየቁት ብርሃኑ ሌንጂሶ፣ “ኦህዴድ እቅዱን የማስቆም ምንም ስልጣን የለውም፣ በፊትም ቢሆን ይህንን ሁሉ ጥናት ያስደረገው የአዲስ አበባ መስተዳድር እንጂ ኦህዴድ አይደለም” ብለዋል።
ማስቆም እንኳን ቢችል የኦሮሚያ ክልል መንግስት እንጂ ኦህዴድ ሊሆን አይችልም ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ የኦህዴድ መግለጫ ግን ቀልድ ካልሆነ በቀር ምንም ሊሆን አይችልም ሲሉ አጣጥለውታል።