ኢሳት (ሰኔ 13 ፥ 2008)
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አስሩም ክፍለ ከተሞች በታክሲ ተራ ማስከበርና በተሽከርካሪ ማፅዳት ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ወጣቶች ያለፍላጎታቸው የገዥው የኢህአዴግ አባል እንዲሆኑ መገደዳቸውን ለኢሳት አስታወቁ።
በየክፍለ ከተሞቹ የሚገኙ የኢህአዴግ ተወካዮች ወጣቶቹ በአባልነት ካልታቀፉና ፎርምን ካልሞሉ በተሰማሩበት ስራ ላይ መቀጠል እንደማይችሉ ሰሞኑ ባካሄዱት ስብሰባ ላይ እንደተገለጸላቸው ወጣቶቹ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ገልጸዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት እነዚሁ ወጣቶች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ሲሉ በራሳቸው ተነሳሽነት ስራቸውን በ1984 አም እንደጀመሩ አውስተዋል።
ይሁንና፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ወጣቶች ስራቸውን እንዲቀጥሉ አስገዳጅ የአባልነት ጥያቄን በቅድመ ሁኔታ በማስቀመጣቸው ምክንያት ፎርሙን ያለፍላጎታቸው እንዲሞሉ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ፎርሙን ተገደን ብንሞላም ልባችን ግን ከፓርቲው ጋር አይደለም ሲሉ የሚናገሩት ወጣቶቹ በተደረገባቸው ጫና እጅግ ማዘናቸውን አክልለው አስረድተዋል።
የብሄራችሁን ማንነት ግለጹ ተብለን ተገደናል በማለት የደረሰባቸውን በደል የገለጹት የከተማዋ ነዋሪዎች ከሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ግብር እንዲካፈሉ መደረጉም አግባብ አለመሆኑን አክለው አስረድተዋል።
አዲስ አበበ ከተማን ጨምሮ በሁሉም ሃገሪቱ ክልሎች በአነስተኛ ጥቃቅን ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የኢህአዴግ አባል እንዲሆኑ መደረጋቸውን ሲገልጹ መቆየታቸውን ይታወሳል።
በከተማዋ በታክስ ደንብ ማስከበር ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ እነዚህ ወጣቶች በተለያዩ ጊዜያት በትራንስፖርት መስጫ አገልግሎት የሚሰራጩ ፖለቲካዊ ውግዘት ያላቸው ወረቀቶች ለፓርቲው ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውንም አስረድተዋል።