የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት መቅረፍ አልቻለም ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 4 ፥ 2009)

በቅርቡ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መስመር አገልግሎት የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር መፍታት ሳይችል መቅረቱን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) ዘገበ።

በከፍተኛ የውጭ ብድር የተገነባው የባቡር አገልግሎት የከተዋን ነዋሪዎች ፍላጎት ማሟላት ባለመቻሉ ምክንያት ተጠቃሚዎች ፊታቸውን ወደ መለስተኛ አውቶቡስ የታክሲ አገልግሎት እያዞሩ መሆኑን የዜና አውታሩ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።

የባቡር አገልግሎቱ መጨናነቅ የበዛበት ከመሆኑን በተጨማሪ የሚሸፍናቸው ቦታዎች ውስንነት በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታን እያስነሳ እንደሚገኝ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረገውን ቃለ-ምልልስ ዋቢ በማድረግ በሪፖርቱ አስፍሯል።

ከአንድ አመት በፊት አገልግሎት የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል የባብሩ መስመር አገልግሎት ከቻይና መንግስት በተገኘ የ475 ሚሊዮን አካባቢ ብድር መገንባቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ፕሮጄክቱ የመዲናዋን የትራንስፖርት ችግር ሙሉ ለሙሉ ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና የከተማዋ ነዋሪዎች ፕሮጄክቱ ችግሩን ከመቅረፍ ይልቅ መፍትሄን ባላገኘው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ላይ ተጨማሪ ጫና ማሳደሩን ለዜና አውታሩ አስረድተዋል።

የባቡር መስመሩ ከነባር የትራንስፖርት አማራጮች ጋር በዲዛይን ስራው እንዲቀናጅ ባለመደረጉ ምክንያት ችግሩ ሊከሰት መቻሉን ደግሞ በኖርዌይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የባቡር ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ ኤሊያስ ካሳ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጸዋል። ከባቡር የሚወርዱ ተገልጋዮች ሌሎች የትራንስፖርት አማራጮችን  ለማግኝነት ብዙ የእግር ጉዞ እንደሚጠበቃቸውና ችግሩ እልባት ካልተሰጠው የባቡር አገልግሎቱ ቅሬታው አብሮት እንደሚዘልቅ አሳስበዋል።

አቶ ዘረያቆብ አሰፋ የተባሉ የመዲናዋ ነዋሪ የባቡር አገልግሎቱን ለማግኘት ብዙ መቸገራቸውና ወዳሰቡበት ቦታ ለመሄድ ሳይችሉ መቅረታቸው ለዜና አውታሩ ገልጸዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት ሃገሪቱ በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ በመሆኗ የባቡር አገልግሎቱን ጨምሮ ሌሎች የልማት ፕሮጄክቶችን ተግባራዊ እየሆኑ እንደሆነ ቢገልጹም እድገቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋና በቅርቡ ሲካሄድ በቆየው ጸረ-መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞ መቀዛቀዝ ሊያሳይ እንደሚችል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስፍሯል።

በመዲናዋ ይኖራሉ ተብለው የሚገመቱ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በባቡር አገልግሎት ተስፋ በመቁረጣቸው ፊታቸው ወደ ቀድሞዎቹ የባለሰማያዊ ቀለም መለስተኛ የአውቶቡስ ታኪሲዎች እያዞሩ ይገኛል ሲል የዜና አውታሩ በአገልግሎት ዙሪያ ባቀረበው ሰፊ ዘገባ አመልክቷል።

የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር አገልግሎት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ አወቀ ሙሉ በበኩላቸው የመዲናዋ አዲስ አበባ ህዝብ በከፍተኛ ቁጥር በመጨመር ላይ በመሆኑ ምክንያት በትራንስፖት አገልግሎቱ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል። ለአገልግሎት ተሰማርተው ከነበሩት 41 ፉርጎዎች መካከል ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ብልሽት አጋጥሟቸው በጥገና ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።