የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተከትሎ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ኢሳት (ታህሳስ 29, 2008)

የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተከትሎ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው ተቃውሞ ትናንትም በተለያዩ አካባቢዎች ቀጥሎ መዋሉ ታወቀ። በትናንትናው ዕለትም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እና በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መንግስት እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ በመቃወም የተለያዩ ህዝባዊ እምቢተኝነቶች መካሄዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በትናንትናው ዕለት የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ 5 ኪሎ ካምፓስ ተማሪዎች ለገና በዓል የተዘጋጀውን ምግብ ባለመመገብ ተቋዉሞአቸውን አሳይተዋል።

በጅማና በተለያዩ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ ተምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች የአውደ-አመት ምግብ ዝግጅቱን ትተው በመውጣት ትብብራቸውን አሳይተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በምዕራብ ሃረርጌ አሰቦት እና ጡጢሳ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ወደጎዳና በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተቃዋሚ አመራሮች የሆኑና በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው እየተለቀሙ መታሰር ጀምረዋል። በእስር ቤተ የሚገኙ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ እህት ወ/ሮ አበዙ ጣፋ በትናንትናው እለት በመንግስት ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል። ከሶስት ቀን በፊት የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር አባል የሆነው በቀለ ገርባ ልጅ ከሚማርበት አዳማ ዩንቨርስቲ ተይዞ መታሰሩ የሚታወስ ነው።

ሁለተኛ ወሩን በያዘው በዚሁ ተቃውሞ፣ ከ140 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ታስረዋል።