የአዲስ አበባ መስተዳድር ዜጎችን የማፈናቀሉን እርምጃ እንዲያቆም የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የአሁኑ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ጠየቀ

ሰኔ ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አብዛሃኞቹ ዜጎች ካርታ ባይኖራቸውም ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውንና የመብራትና ውሃን የመሳሰሉትን አገልግሎቶችን ሲያገኙ እንደነበር ሰመጉ ገልጿል።

“እነዚህ ዜጎች አስቀድሞ ሕጋዊነትን በያዘ መልኩ መኖሪያዎችን እንዲሰሩ መደረግ ነበረበት። ይህ ከሆነ በኋላሕገወጥ ናችሁ በማለት አፍራሽ ግብረኃይል አሰማርቶ በክረምት ነዋሪዎች ላይ ቤት ማፍረስ ኢሰብዓዊ ነው” ሲል ሰመጉ ድርጊቱን በጽኑ ኮንኗል። በ አፍራሽ ግብረኃይሉ ቤቶቻቸው በክረምት ወራት የፈረሰባቸው ዜጎች ቁጥራቸው ከአስር ሽህ እንደሚበልጥና ታዳጊ ሕጻናትና አዛውንት ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ጠቅሷል።

ሰመጉ ሰኔ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ ፣ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት ሕገ መንግሥቱንና ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የፈረመቻቸውን የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ስምምነቶች በተለይም የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳንን በግልጽ የሚጻረር ነው ብሎአል።

ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በደላቸውን በወኪሎቻቸው አማካኝነት ለሰመጉ አሰምተዋል። በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ወረገኑ በሚባል ቦታ ላይ ለበርካታ ዓመታት ቤት ሠርተው፣ ትዳር መሥርተው የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ፈርሰው ቆርቆሮ፣ በርና መስኮታቸው እየተነቃቀለ በአፍራሽ ግብረ ኃይል መወሰዱን ተጎጂዎቹ ማስረዳታቸውንና ሰመጉም ባለሙያዎችን ልኮ ጉዳዩን በአካል በመገኘት ማረጋገጡን አስታውቋል። በተጨማሪም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀጣና 01 መንደር 06 በተለምዶ አጠራር ቀርሳና ኮንቶማ ቁጥራቸው ከ9 ሽህ 617 በላይ አባወራዎች በጠቅላላ 19 ሽህ 624 ነዋሪዎች ከ10 እስከ 15 ዓመት ከኖሩበት ቦታ፣ ‹‹ሕጋዊ አይደላችሁም ቦታው ለቄራ አገልግሎት ስለሚፈለግ ልቀቁ›› እንደተባሉ ሰመጉ ሪፖርት እንደደረሰው ጠቅሷል።

በግጭቱ ለዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ አካል መጉደልና ንብረት መውደም ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ የዜጎች መፈናቀል እንዲያቆም፣ ጉዳዩ በጥንቃቄ ተጠንቶ ካሳ ለሚገባቸው ሁሉ ካሳ እንዲከፈልና ቤታቸው ለፈረሰባቸውና በየቦታው ተበትነው ለሚገኙ ዜጎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ሁሉ ሕጋዊ፣ ሰብዓዊና ቁሳዊ እገዛ፣ እንዲሁም መፍትሔ እንዲሰጧቸው ድርጅቱ ጠይቋል።