ሚያዝያ ፩ (አንድ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ታናሽ ወንድም አቶ ገነቱ ደሳለኝ የሚመራው የአዲስአበባ ከተማ የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አወዛጋቢውን የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን ይፋ አደረገ፡፡ በአዲሱ ደንብ በሚያዝ ሪከርድ መሠረት በተደጋጋሚ አጥፍተዋል የተባሉ አሽከርካሪዎች ፈቃዳቸው ታግዶ የተሀድሶ ስልጠና እንዲወስዱ ይገደዳሉ፡፡
ኤጀንሲው ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን በአዲስዘመን ጋዜጣ መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ.ም ዕትም በከፈለበት ማስታወቂያ ይፋ እንዳደረገው የጥፋት ዓይነቶች በእርከን ለያይቶ አስቀምጧል፡፡
ይህ ደንብ ከአንድ ዓመት በፊት ተግባራዊ ለማድረግ በታሰበበት ወቅት የአዲስአበባ ታክሲ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ በመቃወማቸው ምክንያት ደንቡ ለስድስት ወራት ጊዜ እንዲታገድ ተወስኖ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ የታክሲ አሽከርካሪዎቹ ካነሱዋቸው ነጥቦች መካከል በቂ የሆነ የመኪና ማቆሚያ፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ ደረጃውን የጠበቀ የመኪና መንገድና የእግረኛ መንገዶች በሌሉበት ሁኔታ፣ ይህን ደንብ ተግባራዊ ማድረግ የታክሲ አሽከርካሪዎችን ሆን ብሎ ከስራ ለማስወጣት ካልሆነ በስቀር ትክክለኛ ውሳኔ አለመሆኑን በማንሳት ከደንቡ በፊት የተባሉት ችግሮች መስተካከል ይገባቸዋል የሚሉት ይገኙበታል።
ሆኖም ደንቡ እነኚህ ችግሮች ሳይፈቱ ወደተግባር እንዲገባ መወሰኑ ሌላ ዙር ተቃውሞ ሊያስነሳ ይችላል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል፡፡