የአዲስ አበባ ሕዝብ በገዥው ፓርቲ የበቀል እርምጃ እየተማረረ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ ።

ግንቦት ፪ ( ሁለት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሕዝባዊ እንቢተኝነቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙት የአርሶ አደሮችን መሬት ነጠቃ ከተቋረጠ ወዲህ ገዥው ሕወሃት/ኢህአዴግ ፊቱን ወደ ዋና ከተማዋ መልሷል የሚሉት ነዋሪዎች፤ በልማት ስም ነባር ይዞታያላቸውን የከተማ ነዋሪዎች መሬት መንጠቅ ተጧጡፎ መቀጠሉን ይገልጻሉ።
ነዋሪዎቹ ለኢሳት እንደተናገሩት ካለፍላጎታቸው ከይዞታቸው እንዲነሱ የተደረጉት ነዋሪዎች መኖሪያውን ከመልቀቃቸው አስቀድሞ በመስተዳድሩ ቃል የተገቡላቸው በሙሉ ተፈጻሚ አይሆኑም።
ምትክ ቤት ወይም ምትክ ቦታና የቤት መስሪያ እና የቋሚ ተክሎች ግምት ሳይሰጣቸው እና ሃብት ንብረታቸውን ሳያወጡ በአፍራሽ ግብረ ኃይል አማካይነት በምሽት በላያቸው ላይ ቤታቸው እንዲፈርስ መደረጉን የመዲናዋ ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ።
ልጆቻቸው ትምህርታቸውን ለመጨረስ አንድ ወር ብቻ እየቀራቸው እና መጪው ወራት ክረምት መሆኑ እየታወቀ የዚህ ዓይነት እርምጃ መወሰዱ ከበቀል በቀር ሌላ ስያሜ ሊሰጠው እንደማይችል ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
ከዚህም ባሻገር የከተማዋ መሃንዲሶች በበኩላቸው “ጉቦ ካልሰጣችሁን ጫካ ትጣላላችሁ” ወይም “ምትክ ይዞታ አይሰጣችሁም” በማለት እያስፈራሩዋቸው መሆኑን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
እነኚሁ ወገኖች በቦሌ ክ/ከተማ በገርጂ፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ ቦሌ በሻሌ፣በየረር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ በለቡና ሃና ማሪያም፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ካራ ቆሬና አንፎ ሜዳ ለዘመና የኖሩባቸውን ይዞታቸውን “ ህጋዊእንዲሆንላችሁ በካሬ 3 ሽህ 620 ብር ትከፍላላችሁ፤ ይህን ካልከፈላችሁ ትነሳላችሁ” በመባላቸው ስጋት ውስጥ ይገኛሉ።
አንፎ ሜዳ ላይ በሚባለው አካባቢ መኖሪያ ቤታቸው በክረምት ፈርሶ ቦታቸው ከተወሰደባቸው ከ60 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አንዳንድ ሰዎች በጅብ እንደተበሉና ታንቀው እንደሞቱ ያወሱት ነዋሪዎቹ፤የቀሩትም ለከፍተኛሥቃይና እንግልት ከተዳረጉ በኋላ መልሰው እንዲሰሩ መደረጉ ሲታይ ስርዓቱ ምንም ከማድረግ አይመለስም በማለት ስጋታቸው ከፍተኛ ማለቱን አሳውቀዋል፡፡