ሚያዝያ ፲፫(አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሊቢያ በአሸባሪዎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ለተገደሉት ወጣቶች ኢያሱ ይኩኖአምላክና ባልቻ በለጠ ቤተሰቦች ሀዘናቸውን ለመግለጽ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በማምራት ላይ የነበሩ ወጣቶች ስሜታቸውን
መቆጣጠር ተስኖአቸው ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ውለዋል።
በሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች መንግስትን የሚያወግዙ መፈክሮችን እያሰሙ ወደ ቤተመንግስት በማቅናት ላይ እያሉ ሂልተን ሆቴል አካባቢ በብዛት የተሰባሰቡት የፌደራል ፖሊሶች አስቁመዋቸዋል። ወጣቶች መንግስት ሌባ፣ ደማችን ፈሶ አይቀርም፣ አትነሳም ወይ፣
መንግስት የሌለባት ብቸኛ አገር ፣ መንግስት አይፈልገንም፣ ሉአላዊነት ማለት በውጭ የሚገኙ ዜጎችንም ይመለከታል የሚሉና ሌሎችም የተቃውሞ መፈክሮች ተሰምተዋል። እነዚህ ሰልፈኞች ወደ ሜክሲኮ አካባቢም በመሄድ ተቃውሞአቸዋን አሰምተዋል።
በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መሹዋለኪያ አካባቢ በመሰባሰብ ወደ ጎተራና መስቀል አደባባይ የሚወስደውን መንገድ ዘግተው ውለዋል።
በሁሉም አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት የነበሩ ሲሆን፣ በመጨረሻም ቁጥራቸው ከ50 በላይ ወጣቶችን ወስደው አስረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነገ ሃሙስ በአዲስ አበባ በተጠራው ተቃውሞ ህዝቡ ቁጣውን ይገልጻል ተብሎ ይጠበቃል። በማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን ተቃውሞ እንደሚደረግ የተለያዩ አካላት ማስታወቂያ በህቡዕ እና በይፋ ካያስታውቁ በሁዋላ፣ መንግስት አጋጣሚውን
በመጠቀም ሰላማዊ ሰልፍ መፍቀዱን አስታውቋል። አንዳንድ ወገኖች ደግሞ የስራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ወረቀቶችን እየበተኑ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆነው ሙሃመድ ድሪር ” አንዳንድ አካላት አሁንም በርከት ያሉ ኢትዮጵያዊያን በአይ ኤስ ቁጥጥር ስር ናቸው በማለት የሚያሰራጩት ወሬ ትክክል አለመሆኑን እና ኤምባሲው ባደረገው የማጣራት ስራ በሊቢያ
በአይ ኤስ እጅ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሉም ” ሲሉ ተናግረዋል።
በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በህገ ወጥ ደላሎች ማቆያ ውስጥ እንጂ አይ ኤስ እጅ እንዳልወደቁም አምባሳደር ሙሃሙድ ድሪር ተናግረዋል ሲል የገዢው ፓርቲ ልሳን የሆነው ፋና ዘግቧል።
አንዳንድ ወገኖች እና የውጭ ሚዲያዎች በርከት ያሉ በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በአሸባሪው አይ ኤስ እጅ ናቸው እያሉ የሚያሰራጩት ዘገባ መሰረተ ነው ሲሉም አምባሳደሩ መናገሩን ራዲዮው ዘግቧል።
አምባሳደሩ አንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች እና ግለሰቦች ህዝቡ በድርጊቱ ማዘኑን እና መቆጣቱን በመጠቀም ሁኔታውን ለርካሽ የፖለቲካ መጠቀሚያነት እያዋሉት ነው ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል።
የአምባሳደር ሙሃመድ ንግግር ያበሳጨው አንድ በሊቢያ የሚኖር ኢትዮጵያዊ፣ “አምባሳደሩ በአይ ኤስ እጅ የወደቀ ሰው ስለመኖሩና አለመኖሩ እንዴት አወቀ? ለመሆኑ ሰዎቹ ሲያዙ ያውቅ ነበርን?” ሲል ጠይቋል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን አሁንም በአይ ኤስ እጅ እንደሚገኙ ከተለያዩ ውጭ አገር ዜጎች ማረጋገጡን ተናግሯል
በሌላ በኩል ደግሞ በትሪፖሊ እና ቤንጋዚ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው። በትሪፖሊ በአንድ ቤት ውስጥ ከሚገኙት ዜጎች መካከል እርጉዞች መኖራቸውንም ኢትዮጵያውያን ተናግረዋል።
በቤንጋዚ ኮነሺያ እስር ቤት 37 ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት ውስጥ 8ኛ ወራቸውን ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።