መጋቢት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አስተዳደሩ ባለፉት 11 አመታት ከ143ሺህ በላይ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን በመገንባት በእጣ ማከፋፈሉን ሲገልጽ የቆየ ቢሆንም፣ ቤቶቹ በትክክል ስለመተላለፋቸው በቂ መረጃ አልነበረውም።ይህን ተከትሎ ቆጠራ እንዲካሄድ በተወሰነው መሰረት በ15 ቀናት ቆጠራ ብቻ ከ1 ሺ 200 በላይ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ሳይተላለፉ ለአመታት ተዘግተው የተገኙ ሲሆን ፣98 ቤቶች ደግሞ በማይታወቁ ሰዎች ተይዘው ሲጠቀሙባቸው ተገኝተዋል።
ከ800ሺህ በላይ እጣ ጠባቂ ቤት አልባ ነዋሪዎች ባሉበት ከተማ እየተሰራ ያለው ህገወጥ ስራ የህዝቡ የእለት ተእለት መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖአል።
ህገወጥ ተግባሩ ከአስተዳደሩ አካላት ጋር በመመሳጠር የተፈጸመ ነው ያሉ አንድ ነዋሪ፣ ግለሰቦችን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
የአስተዳደሩ የቤቶች አጀንሲ በእጁ ያሉ ንብረቶችን ማወቅ፣ መመዝገብና ማስተዳደር ሀላፊነት አለበት ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ፣ ይህን ሀላፊነት ያልተወጡ ሹሞች በህግ ሳይጠየቁ ቤት የያዙ ግለሰቦችን ብቻ ማሳደድ ትክክል አይመሰለኝም ብለዋል።
የቤቶች ቆጠራው እስከያዝነው መጋቢት ወር መጨረሻ የሚቀጥል ነው ተብሎአል።