የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖርያ ቤቶችን ጉዳይ በተመለከተ ሕዝቡ ተስፋ እንዳይቆርጥ ያደርጉ ዘንድ ጋዜጠኞችን ተማጸነ፡፡

የካቲት ፴ (ሠላሳ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሕዝቡ በመንግሥት ተስፋ ቆርጦ ገንዘቡን ከባንክ እያወጣ እንደሚገኝም አስተዳደሩ አምኗል፡፡
የአስተዳደሩ የቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሥራ ሃላፊዎች በተለይም 40/60 በመባል የሚታወቀውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንጻዎችከትላንት በስቲያ ለጋዜጠኞች ባስጎበኙበት ወቅት ሕዝቡ በፍጥነት የቤት ባለቤት መሆን ባለመቻሉ ተስፋ እየቆረጠ የባንክ ቁጠባውን እያቋረጠመሆኑን በመጥቀስ ጋዜጠኞች የሕዝቡን ተስፋ ለመመለስ እንዲሰሩ የማግባባት ሥራ አከናውነዋል፡፡
በአስተዳደሩ በኩል የሕዝቡን ተስፋ ለመመለስ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን፣ በቀጣይ ቅዳሜ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከፍተኛ የመንግሥትባለሥልጣናት በሚገኙበት በደማቅ ሁኔታ ለማስመረቅ መታቀዱን በመግለጽ ጋዜጠኞች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡
በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ግንባታቸው ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ ከተባሉት የ40/60 ቤቶች መካከል ከ90 ከመቶ በላይ መጠናቀቅየቻሉት 1290 ቤቶች ብቻ መሆናቸውን ሃላፊዎቹ ተናግረው ፣ ቤቶቹን የሚያስተላልፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ ካልተጠናቀቁ አልረከብም በማለቱ የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና ይህም ሥራ በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ መቶበመቶ ለቆጠቡ 16 ሺህ ቆጣቢዎች በዕጣ ይተላለፋሉ ብለዋል፡፡
1290 ቤቶችን ለመገንባት አምስት ኣመታት ጊዜያትንየፈጀበት አስተዳደሩ በአሁኑ የግንባታ አካሄዱ መቶ በመቶ ቆጥበዋል ላላቸው 16 ሺህ ሰዎች ቤት ለማዳረስ ከ45 ዓመታት በላይ ጊዜንየሚፈልግ መሆኑ ሲታሰብ ቀሪዎቹ ከ120 ሺህ በላይ ሕዝብ ከተስፋ በስተቀር የሚያገኙት ነገር እንደማይኖር መረጃው ያሳያል፡፡፡ በዚህምምክንያት በርካታ ሕዝብ በፕሮግራሙ ተስፋ መቁረጡና ቁጠባውን ማቋረጡ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችአስተየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በመልሶ ማልማት ሥም የሚፈጸመው ማፈናቀል ቀጥሏል።
ከገነት ሆቴል በታች እስከ ቡልጋሪያ አካባቢ በልማት ስም ተነሺዎች “ በአሁኑ ሰዓት የሚሰጠው ግምት እንኳን ተመጣጣኝ ቤት ቀርቶ መሰረት አያሰራም፣ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ አገዛዙ ዜጎቹን እያፈናቀለ ቦታውን ለውጪ ኢንቨስተሮች እየሸጠ የሚሰበስበውን ገንዘብ አንድ አስረኛውን እንኳ ለተፈናቃዩ ዜጋ ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆኑ ፣እንዲሁም ክረምት ሲመጣ እየጠበቀ ዜጎቹን ማፈናቀል መምረጡ ነው “ ሲሉ በምሬት ገልጸዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ “ በየሳምንቱ በሚያስብል ሁኔታ አንዱ ባለስልጣን ሰብስቦ የሚነግረንን በሌላኛው ሳምንት የሚመጣ ባለስልጣን ይሰርዘዋል” ያሉ ሲሆን፣ በመንግስት ሚዲያ ‹‹ በመልሶ ማልማት ሥም የሚደረገው ማፈናቀል የቦታ ካሳ ግምቱን ማስተካከል አስፈላጊነት በመረዳት ፣ አፈጻጸሙ የተፈናቃዩን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ያላገናዘብ በመሆኑ ላልተወሰነ ጊዜ ታግዷል›› ካለ በኋላ፣ ባለፈው ሣምንት ህዝቡን ሰብሰበው ‹‹ በ2009 ዓ.ም አትነሱም፣ ግምታችሁም ይስተካከላል ፣ 155 ሺህ ዝቅተኛ መነሻ የነበረው የካሳ ክፊያ ወደ 244 ሺህ አድጓል- በዚሁ ተመጣጣኝ የሆነ ማስተካከያ ለሁላችሁም ይደረጋል›› ብንባልም እንደገና በሳምንቱ፣ ‹‹ ወደዳችሁም ጠላችሁም፣ ተቀበላችሁም አልተቀበላችሁ የምትቆዩት እስከ ግንቦት 30/09 ብቻ ነው፡›› እንደተባሉ ተናግረዋል።ከዚህ በፊት የምትነሱት ለዩኒቨርስቲና ሆስፒታል ግንባታ ነው ተብሎ ቢነገርንም፣ አሁን ግን ፣ እኛ ተነስተን ቦታውን ከህወኃት ባለሥልጣናት ጋር በሽርክ ለሚሰሩ ለቻይናና ቱሪክ ባለሃብቶች ‹‹ አረቄ ቤት›› ለመገንባት መሆኑን አውቀነዋል ብለዋል። የአዲስ አበባ ነዋሪ ሙሉ በሙሉ ተፈናቃይ የሚሆንበት ጊዜ ቀርቧልና በእኛ የደረሰው እንዳይደርስባችሁ በአንድነት ለመብታችሁ መቆም የህልውና ጉዳይ መሆኑን እንዳትስቱ ሲሉ ለነዋሪዎች ማሳሰቢያ አቅርበዋል፡፡