ሐምሌ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የከተማ ልማትና ኮንስትራክሸን ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው የ40 በ60 የቤት ልማት ፕሮጀክት በቀጣይ ዓመት ከሚካሄደው የአዲስአበባ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫዎች ጋር የተገናኘ መሆኑን ምንጮቻችን ጠቆሙ፡፡
ባለፈው በሒልተን ሆቴል የከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣የአዲስአበባ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ በጋራ ያፋ ያደረጉት ፕሮግራም በአምስት ዓመታት ተከታታይ ጊዜያት ውስጥ የሚገነባውን ቤት ግምት 40 በመቶ ለሚቆጥቡ የኢትዮጽያ ንግድ ባንክ በ17 ዓመታት ጊዜ የሚከፈል የ60 በመቶ ብድር በመስጠት የቤት ባለቤት
ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
በተጨማሪም አነስተኛ አቅም ያላቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች መንግስት በሚሰጣቸው ድጎማ 4 ሺ ብር ገደማ ቆጥበው የባንክ ብድር እንዲያገኙ በማድረግ የስቱዲዮ ቤት ባለቤት እንደሚሆኑ የሚያትት ነው፡፡አንዳንድ ወገኖች ይህ የመንግስት ዕቅድ በቁጠባ መልክ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያልም ብቻ አድርገው እንደሚያዩት ምንጫችን ጠቁሞ ከቁጠባ ው ይልቅ ግን በቀጣዩ ዓመት ለሚካሄደው የአዲስአበባ አስተዳደር ም/ቤት ምርጫ የሕዝብን አስተማማኝ
ድጋፍ ለማግኘት ከወዲሁ ከሚደረጉ ዝግጅቶች አንዱ ነው ብሏል፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በሲቪል ሰርቪሱና በቀበሌዎች አካባቢ በስፋት በያዘው የአንድ ለአምስት አደረጃጀት አማካይነት ኀብረተሰቡን በቀጣይ የመኖሪያ ቤት ችግር
የሚቃለለው ኢህአዴግ በሥልጣን ላይ ሲቆይ ብቻ መሆኑን፣ይህንንም ለማሳካት በ40 በ60 ፕሮግራም እንዲመዘገቡ እየተወተወቱ መሆኑ በቂ ማረጋገጫ ነው ሲል ጠቁሟል፡፡
የአ/አ አስተዳደር ከስምንት ዓመት በፊት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ መጀመሩን፣በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆንም ወደ 400ሺየሚጠጋ ነዋሪ ተመዝግቦ ከዛሬ ነገ ዕጣ ይወጣልኛል ብሎ ሲጠባበቅ የቆየ ቢሆንም በስምንት ዓመታት መገንባትና ማስተላለፍ የቻለው ግን ወደ 70ሺ የሚጠጉ ቤቶችን ብቻ ነው፡፡አስተዳደሩ በየዓመቱ እስከ50ሺ ቤቶችን እገነባለሁ የሚል ዕቅድ ቢኖረውም በተጨባጭ ባለፉት ዓመታት መገንባት የቻለው በዓመት 10ሺ ያህል ቤቶችን መሆኑ ከፍተኛ የአፈጻጸም ድክመት እንዳለበት የሚያሳይ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት ተመዝግበው ከሚጠባበቁት ነዋሪዎች መካከል በስምንት ዓመት ጊዜያት ውስጥ ቤት ማግኘት የቻሉት ከግማሸ በታች መሆናቸው በመንግስት ቁጥጥር ሥር የሚካሄደው ሥራ የቱን ያህል ደካማ እንደሆነ እንደሚያመለክት ምንጫችን አስታውሷል፡፡
ባለፉት ስምንት ዓመታት በዓመት 10ሺ ቤቶችን መገንባት ያልቻለው የአ/አ አስተዳደር በአዲሱ ቤት ልማት ፕሮግራም በቀጣይ 2005 ዓ.ም ብቻ 45ሺ ቤቶችን እገባለሁ በሚል ሕዝቡን ለማማለል የመሞከሩን ጉዳይ ምንጫችን “ ተአሚኒነት የጎደለው፣ትልቅ ውሸት” ነው ሲል አጣጥለውታል፡፡
በኮንዶሚኒየም ፕሮግራም ያልተሳካለትና የሕዝብም ድጋፍ የራቀው የአዲስአበባ አስተዳደር ለሕዝብ አሳቢ መስሎ 40 በ60 በሚባል አዲስ ፕሮግራም የቤት ችግር እፈታለሁ ብሎ መምጣቱ ሕዝብን አጉል ተስፋ እየመገቡ ለማቆየትና የራቀውን ድጋፍ ለማግኘት ብቻ ያለመ፣ የቀጣዩ ምርጫ ዘመቻ አንድ አካል መሆኑን ምንጫችን አስረድቷል፡፡
_____________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide