የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ንግግር የዋና የመነጋጋሪያ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሎአል
(ኢሳት ዜና መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ/ም) ዶ/ር አብይ አህመድ የጠ/ሚኒስትርነት ሹመቱን ሲቀበሉ ያደረጉት ንግግር በማህበራዊ ሚዲያውም ሆነ ከማህበራዊ ሚዲያው ውጭ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በንግግሩ መደሰታቸውን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እየገለጹ መሆኑን ወኪሎቻችን ያደረሱን ሪፖርት ያመለክታል። በተለይ የኢትዮጵአን ታሪክና የአገር አንድነትን አስመልክቶ ያቀረቡት ንግግር ለብዙ ኢትዮጵያውያን የደስታ ስሜት የሰጠ መሆኑን የደረሱን ሪፖርቶች ያሳያሉ። አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ቃል የገቡትን ይፈጽሙ ይሆን የሚለው ጥያቄ እንዳለ ቢሆንም፣ ለጊዜው ብዙዎች ለውጥ ይመጣል ብለው ተስፋ እንዳደረጉ ወኪሎቻችን ገልጸዋል። የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር እስረኞችን በመፍታት ቢታጀብ ኖሮ ልዩ ስሜት ይፈጥር እንደነበር የገለጹ ወገኖች መኖራቸውን፣ ጠ/ሚኒስትሩም ቢቀጥሉት ተከታታይ ቀናት የሚወስዱዋቸው እርምጃዎች ወሳኝ መሆናቸውን ዜጎች አስተያየት ሰጥተዋል።
በማህበራዊ ሚዲያው በተለይም በፌስቡክ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር በበጎ ጎኑ ተቀብሎታል። አብዛኛው አስተያየት ሰጪዎች ጠ/ሚኒስትሩ ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ እንዲያሳዩ እየወተወቱ ነው።
አርበኞች ግንቦት7 ተስፋ ሰጪ የሆነው የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር በተግባር ተተርጎሞ ማየት እንደሚሻ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። “ ከህወሓት/ኢህአዴግ ድርጅታዊ ባህል ውጭ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የአገራችን ኢትዮጵያን ዝናና ክብር ከፍ የሚያደርጉ፤ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ፤ ፍቅርና ስምምነትን የሚሰብኩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። “ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ የሚተጉ ልጆችን አፍርታለች። ልጆቿም ወደቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምና ፍትህ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ እድልኦ ለመላው ዜጎች ይደረስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ፤ ይደክማሉ” በማለት ሀገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ መስማት የናፈቀውን አባባል ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ንግግር ባለተሰማበት ፓርላማ ውስጥ ተናግረዋል።” በማለት የገለጸው አርበኞች ግንቦት7፣ እነዚህን ተስፋ ሰጪ ንግግሮች ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት መስማት አጅግ በጣም የሚያበረታታ ቢሆንም፣ እነዚህ ተስፋዎች በንግግር ብቻ የምንሰማቸዉ ሳይሆኑ በቶሎ በተግባርም መተርጎም አለባቸዉና በቅርቡ አብረን የምናያቸዉ ይሆናሉ” ብሎአል።
“ዶ/ር አቢይ በፀጥታ ኃይሎች ሕይወታቸው ለተቀጠፉ ወገኖቻችን የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን ገልፀዋል፤ ይቅርታም ጠይቀዋል። ለወደፊቱም ተመሳሳይ የመብት ጥሰት እንዳይፈፀም ስለእርቅ ተናግረዋል፤ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እንደሚደረግ፤ በአጠቃላይ በህገመንግሥቱ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ መብቶች ሁሉ መከበር እንደሚኖርባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።” የሚለው አርበኞች ግንቦት7፣ “ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ባለፈዉ የካቲት ወር አጋማሽ የታወጀዉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የዜጎችን መሠረታዊ መብትና ነጻነት የሚቀማና በተወሰነ መልኩ ህገ መንግስቱንም የሚያግድ በመሆኑ፣ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር የዜጎች መሰረታዊ መብትና ነጻነት እንዲከበር ለማድረግ የሚያስችሏቸዉን ዕርምጃዎች በአጭር ግዜ ዉስጥ ይወስዳሉ ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።
“ዲሞክራሲ ያለነጻነት አይታሰብም። ነጻነት ከመንግስት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም። ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንዱ ሰው የተፈጥሮ ጸጋ እንጂ” በማለት ዶክተር አቢይ አህመድ የገለጹት ሰፊ ተቀባይነት ያለው ጽንሰ ሀሳብ እንዴት ተግባራዊ ሊደረግ እንደታሰበ አርበኞች ግንቦት 7 ማወቅ እንደሚሻም በመግለጫው ጠቅሷል።
“የዶ/ር አቢይና ባልደረቦቻቸው ጥረት የኢትዮጵያን ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ከሆነ አርበኞች ግንቦት 7 አጋራቸው ነው። ይሁን እንጂ ከፍላጎቶች ባለፈ ተጨባጭ የተግባር ጥረቶችን ማየት ይሻል።” የሚለው ንቅናቄው፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካቢኔያቸውን እንዳቋቋሙ የመጀመሪያ ስራቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታትና ከፖለቲካና የሲቪል ማኅበራት ጋር መምከር መጀመር” መሆን አለበት ብሎአል።
የአፍሪካ ቀንድ የሂማውንራይትስ ሊግ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ዶ/ር አብይ በንግግራቸው የህሊና እስረኞች እንደሚፈቱ አለመናገራቸው ቅር እንዳሰኘው ገልጿል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ 15 ሺ የሚሆኑ ዜጎች መታሰራቸውን የገለጸው ሊጉ፣ ከሰው ተገለው የታሰሩትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች በመፍታት ድርጅታቸው ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብት መከበር ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያሳይ እንዲሁም ከሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ውይይት እንዲጀምር ጠይቋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጨምሮ ሌሎችም አፋኝ ህጎች እንዲነሱም ድርጅቱ አሳስቧል።