የአውስትራሊያ መንግስት ኢትዮጵያውያን የማደጎ ልጆች ወደ አገሩ እንዳይገቡ ከለከለ

ሰኔ ፳፫ (ሃያ ሶስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአውስትራሊያ መንግሥት በማደጎ (ጉዲፈቻ ) ሥም፣ ወደ አውስትራሊያ ይመጡ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ይፈቅድ የነበረውን ሕገ ደንብ መሰረዙን የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቁ።

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኒኮላ ሮክሶን ባለፈው ሃሙስ  ይህንኑ አስመልክቶ እንደተናገሩት፤- የአውስትራሊያ መንግስት ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የተገደደው ከኢትዮጵያ በማደጎ ስም የሚመጡ ሕፃናት ጉዳይ ብዙ ችግሮች ያስከተለና፣ ውስብስብ እየሆነ ስለመጣ ነው” ሲሉ ገልፀዋል።

ይህንኑ የአውስትራሊያ መንግስትን ውሳኔ፣ ሕፃናቱን በማስመጣት ስራ ላይ የተሰማሩና ጥቅማቸው የሚቀርባቸው አውስትራሊያ በቀል ድርጅቶች፣ ከወዲሁ እየተቃወሙት ሲሆን መንግስት ውሳኔውን እንደገና እንዲመረምር እንጠይቃለን እያሉ እንደሆነም ታውቋል።

የአውስትራሊያ መንግስት እ.ኤ.አ በ2009 እና በ2010 በማደጎ ስም ወደ አገሩ የሚመጡትን ኢትዮጵያውያን ሕፃናት በተመለከተ፣ የኢህአዴግ ስርዓት ትግራይ ውስጥ እየተደረገ ላለው የልማት እንቅስቃሴ የአውስትራሊያ መንግስት ድጋፍ ያደርግ ዘንድ በግልፅ ከመጠየቅ አልፎ እንደ ቅድመ ሁናቴ በማስቀመጡ፤ የአውስትራሊያ መንግስት ይህ ከፕሮግራሙ አላማ ጋር ፈፅሞ የሚጣረስ መሆኑን በመግለጽ ላልተወሰነ ጊዜ ኢትዮጵያውያን የማደጎ ልጆች ወደ አገሩ እንዳይገቡ እገዳ ጥሎ ነበር።

እንደሚታወቀው ልጅ ማግኘት የተሣናቸው ምዕራባውያን፣ በርካታ ገንዘብ በማውጣት በጉዲፈቻ የሚያሳድጓቸውን ህጻናት ከአፍሪካና ከእስያ የሚወስዱ ሲሆን፤ በዚህ በኩል  ኢትዮጵያውያን የማደጎ ሕፃናት ከቻይናውያን በመቀጠል በዓለማችን ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛሉ።

ባብዛኛው ኢትዮጵያውያን ጨቅላዎችን ለውጭ አገር ሰዎች በማደጎ ስም የሚደረገው ሽያጭ፣ ሕፃናቱ ወላጆቻቸው በህይወት ሳሉ፣ እንደሞቱ የሚያረጋግጥ በፍርድ ቤት በተወሰነ ሃሰተኛ ሰነድ ጭምር የሚደገፍ ሲሆን፤ “ልጆቻችሁ አሜሪካ ሄደው እንዲማሩላችሁ ነው፤ ተምረው ሲጨርሱ ወደ አገር ቤት በመመለስ ይረዷችኋል፣ እዚያም ሳሉ በስልክም ሆነ ትምሕርት ቤት ሲዘጋ መጥተው ይጠይቋችኋል… ወዘተ እየተባለ፣ ችግር ያጎሳቆላቸው እናቶችን በማታለልና፣ በትንሽ ገንዘብ በመደለል የሚሰራ ከፍተኛ የማጭበርበር ስራ ነው።

በዚህ መልኩ ሕፃናት ልጆቻቸውን የተነጠቁና፣ ልጆቻቸው የት አገር እንደሚኖሩና በምን ሁናቴ ላይ እንዳሉ የማያውቁ እናቶች በኢትዮጵያ ምድር የሚያሰሙት እሮሮና ለቅሶ የሚያባራ አልሆነም። ሕፃናቱም ቢሆኑ አፍ ሲፈቱና ነፍስ ሲያውቁ በውስጣቸው እያደገ የሚመጣው የማንነት ጥያቄ እያስገደዳቸው፤ የሚያውቁትን ሃቅ ፍርጥርጥ አድርገው ማውጣታቸው ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ያለ ነገር ነው። በዚህ በኩል ታዋቂዋ የሆሊውድ አክተር አንጀሊና ጆሊ ላይ የደረሰው በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው።

የአገራችን ሕፃናት ላይ አስነዋሪ የወሲብ ጥማታቸውን ለመወጣት በጉዲፈቻ ስም የሚወስዱ በርካታ አሳዳጊዎች እንዳሉም በተደጋጋሚ የምንሰማው ዜና ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ አቅሙ ሳይኖራቸው ሕፃንቱን እናሳድጋለን ብለው በመውሰድ ለባሰ ችግር ያጋለጡም እንዳሉ አይዘነጋም።

በዚህ በኩል አሜሪካ ውስጥ ከአሳዳጊዎቿ ጋር ትኖር የነበረችው የ13 ዓመቷ ኢትዮጵያዊ የማደጎ ሕፃን ሃና ዊልያምስ፣  ባለፈው ዓመት በደረሰባት ረሃብ የተነሳ ሕይወቷ ማለፉ ሃኪሞች ማረጋገጣቸው የቅርብ ጊዜ አሳዛኝ ትዝታችን ነው።

በአሁኑ ሰዓት ከ 63 በላይ ድርጅቶች ከኢህአዴግ መንግስት ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው በዚሁ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣  ከነዚህም መካከል  በቀድሞ የሕወሃት ታጋዮች ፊታውራሪነት የሚንቀሳቀሱት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

በአገራችን አንድን ኢትዮጵያዊ ሕፃን ወስዶ ለማሳደግ የሚፈልግ የውጭ አገር ዜጋ፣ ሌላውን ወጭ ሳይጨምር ከ20 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2011 1ሺህ 732 ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ወደ አሜሪካ የተጋዙ ሲሆን፣   በ2010 ደግሞ ከአገር ከወጡት 4 ሺህ 200 ያህል ሕፃናት መካከል፣ ከ2ሺህ 500 የሚሆኑት በህጋዊ ደላሎች አማካኝነት ወደ አሜሪካ መወሰዳቸውን በወቅቱ የወጡ ሰነዶች ያመላክታሉ በማለት ቅዱስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል::

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide