ኢሳት (ሚያዚያ 21 ፥ 2008)
የአውስትራሊያ መንግስት የዛሬ 15 ቀን በጋምቤላ ክልል ከ208 ሰዎች በላይ መገደላቸውንና 108 ህጻናትና ሴቶች መጠለፋቸውን ተከትሎ፣ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ማሳሰቢያ አወጣ። የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይና ንግድ ሚኒስትር በመግለጫው እንዳመለከተው፣ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ለማድረግ እቅድ ያላቸው አውስትራሊያውያን ለጉዞ ከመዘጋጀታቸው በፊት የጉዞውን አስፈላጊነት መመርመር እንደሚገባቸው ገልጿል።
የአልሻባብ አሸባሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የመንግስት ህንጻዎች፣ ታሪካዊ ቦታዎችና የውጭ ዜጎች በሚያዘወትሩባቸው ስፍራዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን መረጃ እንደደረሰውም የአውስትራሊያ መንግስት የውጭ ጉዳይና ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው በዚሁ መግለጫ አስታውቋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በማንኛውም ሰዓት ሊደርስ የሚችለውን የሽብርተኝነት ጥቃት በመገንዘብ የአውስትራሊያ ዜጎች ወደኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ማሳሰቡ በዚሁ ትናንት በወጣው ማሳሰቢያ ላይ ተመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ከማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ሲደረግ የቆየው ተቃውሞ በማንኛውም ሰዓት ሊያገረሽ ስለሚችልና በአካባቢውም አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ባለመኖሩ አውስትራላውያን ወደኦሮሚያ ክልልና አካባቢው እንዳይጓዙ በማሳሰብ፣ ዜጎቹ ተቃውሞ ወደሚካሄድባቸው ስፍራዎች እንዳይጓዙ የአውስትራሊያ መንግስት የውጭ ጉዳይና ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው በዚሁ መግለጫ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም በሚደረጉ ታላላቅ ስብሰባዎችን ዜጎቹ እንዳይሳተፉ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ የሚጓዙበት አካባቢ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ማረጋገጫ ካላገኙ አደጋ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
በተለይም በአዲስ አበባ የመርካቶ አካባቢ፣ የሱማሌ ክልልና ድንበር አካባቢዎች፣ የኤርትራና ሱዳን ድንበር አካባቢዎች፣ የኬንያና የደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢዎች፣ የጋምቤላ፣ በአፋር ክልሎች፣ የጸጥታ ችግር ያለባቸው በመሆናቸው ዜጎቹ በተጠቀሱት አካባቢዎች እንዳይጓዙ የአውስትራሊያ መንግስት የውጭ ጉዳይና ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የካናዳ መንግስት በኤርትራ፣ በሱማሌ፣በኬንያ፣ በሱዳና ደቡብ ሱዳን የድንበር አካባቢዎች ዜጎቹ እንዳይጓዙ ጠቅሶ፣በጋምቤላ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል በአምቦ አካባቢም ዜጎቹ እንዳይጓዙ አሳስቧል።