ኢሳት (ጥር 11 ፥ 2008)
የአውሮፓ ፓርላማ በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና በኢትዮጵያ አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ለመምከር ሃሙስ ልዩ የውይይት መድረክ ሊያካሄድ መሆኑን ይፋ አደረገ።
ከ700 በሚበልጡ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት የሚካሄደው ይኸው ውይይት የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለው እንደሆነም ተገልጿል።
በአውሮፓ ፓርላማ አባላት ዘንድ ሃሙስ በብራሰልስ የሚካሄደው ይኸው ልዩ መድረክ የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር የሆነው የአውሮፓ ህብረት አሳሳቢ ናቸው ባላቸው የሰብዓዊ መብት አያያዞች ዙሪያ አቋሙን የሚያንጸባርቅበትን ሂደት እንደሆነም ከህብረቱ የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ተቃውሞና፣ የፀጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያሉት እርምጃ እንዲሁም የጸረሽብር ህጉ የሚያመጣው ተፅዕኖ በፓርላማ አባላቱ ዘንድ ሰፊ ውይይት ይካሄድበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በልማት ስም ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይና የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም 751 በሚሆኑ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ዘንድ አበይት የመወያያ መድረክ ርዕስ እንደሚሆኑም ህብረቱ በድረ-ገፅ ካሰፈረው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
የአውሮፓ ህብረት አባል የሆኑ ከ20 በላይ ሃገራት በሚካፈሉበት በዚሁ የመወያያ መድረክ ኢትዮጵያን የተመለከቱ በርካታ ፖለቲካዊና የሰብዓዊ መብት አያያዞችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚቀርቡም ታውቋል።
በፓርላማ አባላቱ ዘንድ ለውይይት የቀረቡ መረጃዎችም ድምፅ ተሰጥቶባቸው የአውሮፓ ህብረት እርምጃዎችን እንዲወስድ የሚያደርግ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን በማስጠራት በወቅታዊ የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ማብራሪያ እንዲሰጡ ማድረጉም ይታወሳል።
ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የአውሮፓ ህብረት ዝምታውን በመስበር በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እርምጃን እንዲወስድ ዘመቻ መክፈታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።